Sewasew History

Sewasew History

You may also like

Mesi
Mesi

Bringing Africa's knowledge to the Internet!

Sewasew is a multilingual social network platform that is meant to document Africa from head to toe the indigenous way! We aspire to be the go-to site to share and know about anything that's Africa.


“How would that be possible?” you may ask. Well, Sewasew believes that every individual’s gotta have good knowledge about some aspect of Africa, and if there is a platform, equipped with all the nece

09/11/2023

09/08/2023

ከመቶ አመት ብኋላ የደረሰው ደብዳቤ
====
ምን ያደርጋል ፖስታ ነጋዴ ‘ሚያመጣው

መገናኘት ነበር ናፍቆት የሚያወጣው።

ይላል ይርዳው ጤና በአንድ ዘፈኑ የደብዳቤን የልብ አለማድረስ እና የናፍቆቱን ልክ ሲገልጽ። ነጋዴ የሚያመጣው ማለቱ ድሮ ደብዳቤ በሲራራ ነጋዴ አማካኝነት ይላክ ስለነበር ነው። እዬዬም ሲዳላ አይደል? እሼ ከተላከ ከአንድ ምዕተ አመት ብኋላ የሚደርስን ደብዳቤስ ምን ይሉታል? ቢቢሲ ዛሬ ባወጣው ዜና ዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ በ1916 እንደ ፈረንጆቹ የዘመን አቆጣጠር የተላከ ደብዳቤ ከ100 ዓመት በላይ ዘግይቶ ደረሰ ይለናል። አጀብ ነው! ይሄኔ እኮ ደብዳቤው መልስ የሚያሻ አስቸኳይ ጉዳይ ያለበት ሊሆንም ይችላል። የቁራ መልዕክተኛ እጅ ወደቀ እንጂ።

የንጉሥ ጆርጅ አምስተኛ ምስል ያረፈበት ባለ አንድ ፓወንድ ቴምብር የተለጠፈበት ፖስታ ከአንድ መቶ ዓመት በላይ ቆይቶ ክሪስታል ፓላስ ሐምሌት መንገድ ላይ ከሚገኘው የግሌን ፊንሌይ መኖሪያ ሕንጻ ደርሷል።

“ደብዳቤው ከአንድ መቶ ዓመት በላይ እንዴት ሊዘገይ እንደቻለ መደነቅ እና ግራ መገባት ተሰምቶናል” ሲል ደብዳቤውን የተቀበለው ግሌን በሁኔታው የተሰማውን ተናግሯል።

የአገሪቱ የፖስታ አገልግሎት ድርጅት ሮያል ሜይል ስለጉዳዩ በሰጠው ምላሽ “ይህ ደብዳቤ ምን እንዳጋጠመው እርግጠኛ አይደለንም” ብሏል።

ደብዳቤው ባለፈው ዓመት ያረፉት የንግሥት ኤልዛቤት አባት ንጉሥ ጆርጅ አምስተኛ በዙፋን ላይ በነበሩበት እና የመጀመሪያው የዓለም ጦርነት በተካሄደበት ጊዜ ነበር የተላከው።

ደብዳቤው በተላከበት አድራሻ አሁን ላይ ኗሪ የሆነው የ27 ዓመቱ ወጣት የቲያትር ዳይሬክተር ደብዳቤውን ከተቀበለ ብኋላ ምንም እንኳን አንድ ሰው በስሙ ያልተላከ ደብዳቤን ከፍቶ ማንበብ ወንጀል ቢሆንም ደብዳቤውን ከፍቶ ለማንበብ መጓጓቱን ተናግሯል። “ይህንን በማድረጌ ወንጀል የምፈጽም ከሆነ፣ ማድረግ የምችለው ይቅርታ መጠየቅ ብቻ ነው።” ብሏል ግሌን።

ደብዳቤው የተላከለት ግለሰብ ወይም ቤተሰብ አባላት በህይወት ካሉ ይህ ትልቅ ታሪካዊ ማስታወሻ ይሆናል።

09/05/2023

ፈረሱን ካህን ያደረገው ንጉሥ
=====
ሮም ኃያል በነበረችበት ዘመን ከነበሯት ገዢዎች አንዱ ጋየስ(Gaius) ነበር። ይህ ገዢ ካሊጉላ (Caligula) በሚባል በተሰኘ ስሙ የበለጠ ይታወቃል። ጥንታዊ የታሪክ ደራሲያን እንደሚነግሩን ካሉጉላ ፈረሶች ከሰው አብልጦ ይወድ ነበር። ታዲያ ካሊጉላ ከፈረሶቹ ሁሉ አብልጦ የሚወደው Incitatus (ኢንሲታተስ?) የተባለ ፈረሱን ነበር። ለዚህ ፈረስ የማይደረግለት አይነት እንክብካቤ አልነበረም። እንደ ፈረስ ሳይሆን እንደ ልዑል ነበር ሞግዚቶቹ የሚንከባከቡት። ጌጣጌጡ ልዩ ነበር፣ የራሱ ቤትም ነበረው። የምግቡ ነገር ከተነሳ ደግሞ ግርምትን የሚፈጥር ነው ። የኢንሲታተስ ምግብ በጥንቃቄ የተመረጠ ሆኖ ከወርቅ ቅንጥብጣቢ ጋር ተቀላቅሎ ነበር የሚቀርብለት።

ስለዚህ ገዢ እና ስለፈረሱ ታሪክ አስገራሚው ነገር ግን ወርቅ መመገቡ አልነበረም። ካሊጉላ በፈረሱ ፍቅር አቅሉን ከመሳቱ የተነሳ በአንድ ወቅት ኢንሲታተስን (ፈረሱን) የሮም ሴናተር ለማድረግ እስከመሞከር ደርሶ ነበር። የኋለኛው ይባስ አይደል የሚባለው? በመጨረሻም ካሊጉላ ፈረሱን ካህን አድርጎ አረፈው። ኢንሲታተስ ካህን ነው አለ ካሊጉላ! ንጉስም አይደል ማን ይክሰሰው?

09/02/2023

ሊየተናል ጄኔራል ነጋ ኃይለሥላሴ
===
መቸም ጀግናና ጀግንነት ሲነሱ የሚያስነሱት ርእስና ርእሰ ጉዳይ የዋዛ አይደለም። የቱን ጥዬ፣ የቱን ይዤ … እስኪባል ድረስ ነው የሚያስጨንቁት። የዚህ ምክንያቱ ደግሞ ጀግንነትም ሆነ ጀግናነት (ጀግና መሆን) በቀላሉ ፊጥ የሚባልበት ባለመሆኑና እስከ ሕይወት መስዋዕትነት ድረስ የሚዘልቅ ተግባር መፈፀምን ስለሚጠይቅ ነው። ይህ ሁሉ የሚሆነው፣ የሚወደሰውና ከባለ ውለታነት ተርታ የሚያሰልፈው የጀግንነት ውሎውና ተግባሩ ለአገርና ለሕዝብ እስከሆነ ድረስ ነውና የዛሬውን ባለውለታችንን ከዚሁ አኳያ የምናነሳቸው ይሆናል።

ሊየተናል፡ጄኔራል፡ ነጋ፡ ኀይለ፡ ሥላሴ ይባላሉ፤ በሌላኛው (በጀግንነት) ስማቸው ደግሞ አባ፡ ይባስ።

ሊየተናል፡ ጄኔራል፡ ነጋ፡ ተጽፎም ሆነ ተነግሮ የማያልቅ ታሪክ ባለቤት ናቸው። ያልወጡት ዳገት፤ ያልወረዱት ቁልቁለት የለም። ይሁን እንጂ በዚህ አንድ ገፅ ጋዜጣ ሁሉንም ቀርቶ የሰናፍጭ ቅንጣት ያህሏን ታሪካቸውን እንኳን ልናወራላቸው አንችልም። በመሆኑም፣ ያለን አማራጭ አንባቢ ስለ ባለታሪኩ ሰነዶችን በማገላበጥ ገድላቸውን መገንዘብ ያለበት መሆኑን መጠቆም ነው።

ትውልድና፡ እድገት

ሊየተናል. ጄኔራል፡ ነጋ፡ ኀይለ፡ ሥላሴ ካባታቸው፡ ከልጅ፡ ኀይለ፡ ሥላሴ፡ ሞላ ከናታቸው፡ ከወይዘሮ፡ ደስታ፡ አባዬ የይፋት፡ አውራጃና፡ የመንዝ፡ አውራጃ፡ አዋሳኝ፡ በሆነው ጎራት፡ አካባቢ ሚያዝያ፡ 30፡ ቀን፡ 1910 ዓ.ም.፡ ተወለዱ።

ልጅ፡ ነጋ፡ ኀይለ፡ ሥላሴ፣ አብዛኛውን፡ የሕፃንነትና፡ የልጅነት፡ ዘመናቸውን፡ ይፋት፡ (መንግሥት፣ ጎራት፣ ዐማች፡ ዐምባ፣ ቍጫጭ፡ ዐምባ፣ ቆቦ)፡ አሳለፉ።

ትምህርት

በጥንታዊው፡ የኢትዮጵያ፡ ልማድ፣ አራት፡ ዓመት፡ ካራት፡ ቀን፡ ሲሞላቸው፣ ደብተራ፡ ገብረ፡ ክርስቶስ፡ ዘንድ፣ ቀጥሎም፡ አጎታቸው፡ አለቃ፡ ገብረ፡ ክርስቶስ፡ ዘንድ፣ እንዲሁም፡ መምህር፡ ተቀጥሮላቸው፣ ከፊደል፡ መቍጠር፡ እስከ፡ ዳዊት፡ መድገም፡ ያለውን፡ ባህላዊ፡ የቀለም፡ ትምህርት፡ ባስደናቂ፡ ፍጥነት፡ አጠናቀቁ። በጊዜው፡ ለጨዋ፡ ልጅ፡ ኹሉ፡ ይሰጥ፡ የነበረውንም፡ የሥርዐት፣ የጠመንጃ፡ ተኩስ፣ የውሃ፡ ዋና፣ የፈረስ፡ ግልቢያና፡ የመሳሰለውን፡ ትምህርት፡ አገኙ።

በ1917 ዓ.ም፣ ልጅ፡ ነጋ፡ ኀይለ፡ ሥላሴ፣ ከወንድሞቻቸው፡ ከልጅ፡ አሰፋ፡ ኀይለ፡ ሥላሴና፡ ከልጅ፡ ለማ፡ ኀይለ፡ ሥላሴ፡ ጋራ፣ እናታቸውን፡ ወይዘሮ፡ ደስታ፡ አባዬን፡ ተከትለው፣ በሕይወት የሌሉትን ያባታቸው (ኀይለ፡ ሥላሴ፡ ሞላ)ን የወግ፡ ዕቃ፡ ለመንግሥት፡ ለማግባት፣ አዲስ፡ አበባ፣ ራስ፡ ተፈሪ፡ መኰንን፡ ዘንድ፡ ቀረቡ። ልጅ፡ ነጋ፡ ኀይለ፡ ሥላሴ፣ ራስ፡ ተፈሪ፡ መኰንን፡ በዚህ፡ ዕለት፡ ለመጀመሪያ፡ ጊዜ፡ አዩአቸው፤ ስላባታቸውም፡ ማረፍ፡ የገለጹላቸው፡ የሐዘን፡ ስሜትና፡ የማጽናናት፡ ቃል፡ በልጅነት፡ አእምሯቸው፡ ለመቼውም፡ ተቀርጾ፡ ኖረ።

ራስ፡ ተፈሪ፡ መኰንን፣ የልጅ፡ ኀይለ፡ ሥላሴን፡ ልጆች፡ ማስተማር፡ የኛ፡ ተግባር፡ ነው፡ ቢሉም፣ የልጆቹ፡ ዕድሜ፡ ማነስ፡ ከቤተሰብ፡ ርቆ፡ ለመኖር፡ ስላልፈቀደ፣ ከሁለት፡ ዓመት፡ በኋላ፡ ከይፋት፡ ይዘዋቸው፡ እንዲመጡ፡ ወይዘሮ፡ ደስታን፡ ዐደራ፡ አሉ።

ይፋት፡ ተመልሰው፣ ሁለት፡ ዓመት፡ እንደ፡ ሞላም፣ በ1919፡ ዓ.ም.፣ የልጅ፡ ኀይለ፡ ሥላሴ፡ ማኅበርተኞች፣ እነደጃዝማች፡ አበበ፡ አውራሪስ፣ ልጅ፡ (ዃላ፣ ቢትወደድ)፡ መኰንን፡ እንዳልካቸው፣ ልጅ፡ መኵሪያ፡ ይገባሻል፣ ባላምባራስ፡ (ዃላ፣ ራስ)፡ አበበ፡ አረጋይ፣ ነጋድራስ፡ አበበ፡ ድረስ፣ ልጅ፡ ኀይለ፡ ማርያም፡ ገዝሙ፡ አንድጋ፡ ኾነው፣ “ዐልጋ፡ ወራሽ፡ ራስ፡ ተፈሪ፡ መኰንን፡ ባዘዙት፡ መሠረት፣ ልጆችዎ፡ ትምህርት፡ ቤት፡ እንዲገቡ፡ ወዳ አዲስ፡ አበባ፡ ይላኳቸው”፡ የሚል፡ ማስታወሻ፡ ደብዳቤ፡ ለወይዘሮ፡ ደስታ፡ ጻፉላቸው። ከጥቂት፡ ወራት፡ በዃላ፣ ሦስቱ፡ ወንድማማቾች፡ (ልጅ፡ ነጋ፣ ልጅ፡ አሰፋ፣ ልጅ፡ ለማ፡ ኀይለ፡ ሥላሴ) አዲስ፡ አበባ፡ እንደ፡ መጡ፥ ካባታቸው፡ ማደሪያ፡ በደጃዝማች፡ ይገዙ፡ በሀብቴ፡ በኩል፡ እየተሰበሰበ፥ በወር፡ 30፡ ብር፡ እንዲከፈልላቸው፡ ሆኖ፣ እተፈሪ፡ መኰንን፡ ትምህርት፡ ቤት፡ ባአዳሪነት፡ ተመዝግበው፣ ዘመናዊ፡ ትምህርታቸውን፡ በፈረንሳይኛ፡ ቋንቋ፡ ለሰባት፡ ዓመት፡ ተከታተሉ።

ሦስቱም፡ ወንድማማቾች፡ እጅግ፡ ብሩህ፡ አእምሮ፡ ነበራቸውና፣ በመጀመሪያው፡ ዓመት፣ ያንደኛ፡ ደረጃ፡ ትምህርታቸውን፡ ባስደናቂ፡ ውጤት፡ አጠናቀው፣ ባምስተኛው፡ ዓመት፡ ልጅ፡ አሰፋ፡ ኀይለ፡ ሥላሴ፣ በሰባተኛው፡ ዓመት፡ ደግሞ፣ ልጅ፡ ለማና፡ ልጅ፡ ነጋ፡ ኀይለ፡ ሥላሴ፡ የሁለተኛ፡ ደረጃ፡ መፈጸሚያና፡ የዩኒቨርሲቲ፡ መግቢያ፡ “ባካሎሬያ፡ ሲያንቲፊክ”፡ ፈተናቸውን፣ በ1924ና፡ በ1926 ዓ.ም. መጨረሻ፣ በ”ፍጹም፡ ጥሩ”፡ (“ኤክሰለንት”)ና፡ በ”እጅግ፡ ጥሩ”፡ (“ትሬ፡ ቢየን”)፡ ማዕርግ፡ አልፈዋል። ይኸውም፡ የባካሎሬያ፡ ፈተና፡ በኢትዮጵያ፡ ለመጃመሪያ፡ ጊዜ፡ መካሄዱ፡ ነበር። በዚሁ፡ ብልህነታቸው፣ እንዲሁም፡ በትሕትናቸውና፣ በግብረ፡ ገብነታቸው፣ አስተማሪዎቻቸውም፡ ሆኑ፡ የተማሪ፡ ቤት፡ ጓደኞቻቸው፡ በተለይ፡ ወደዷቸው፣ አከበሯቸው፣ ተመኩባቸውም፤ “የተፈሪ፡ መኰንን፡ ኮከቦች”፡ የሚል፡ ማቈላመጫ፡ ስምም፡ አወጡላቸው። ልጅ፡ ነጋ፡ ኀይለ፡ ሥላሴ፣ በሒሳብ፣ በሳይንስ፣ በሥዕልና፡ በሙዚቃ፡ የተለየ፡ ስጦታ፡ ነበራቸው። ባአዲስ፡ አበባ፡ ትምህርት፡ ቤቶች፡ መካከል፡ በተደረጉ፡ የሙዚቃም፡ የሥዕልም፡ ውድድሮች፣ አንደኛ፡ እየወጡ፣ ከንግሥተ፡ ነገሥታት፡ ዘውዲቱ፡ እጅ፡ ሽልማትን፡ ተቀብለዋል።

ባካሎሬያቸውን፡ አግኝተው፣ ለከፍተኛ፡ ትምህርት፡ ወደ፡ አውሮፓ፡ እንዲሄዱ፡ መወሰኑ፡ ሲነገራቸው፣ “ፋሺስት፡ ኢጣሊያ፡ ኢትዮጵያን፡ ለመውረር፡ እየተሰናዳች፣ አገሬን፡ ጥዬ፡ አልሄድም”፡ ብለው፣ ወደ ጦር፡ ትምህርት፡ ቤት፡ ለመግባት፡ ያላቸውን፡ ፍላጎት፡ ገለጹ። ጦር፡ ትምህርት፡ ለመግባት፡ የዕድሜያቸው፡ ማነስ፡ እንደማይፈቅድላቸው፡ ቢነገራቸውም፣ ለግርማዊነታቸው፡ አመልክተው፣ ከስድስት፡ ወር፡ ጥበቃ፡ በኃላ፣ በልዩ፡ ፈቃድ፣ በጥር፡ ወር፡ 1927፡ ዓ.ም እገነት፡ ሆሎታ፡ ቀዳማዊ፡ ኀይለ፡ ሥላሴ፡ ጦር፡ ትምህርት፡ ቤት፡ ገብተው፣ ከትምህርቱ፡ ተሳተፉ።

በስዊድን፡ ወታደራዊ፡ ተልእኮ፡ በፈረንሳዊ፡ ቋንቋ፡ የተሰጠው፡ የጦር፡ ትምህርት፡ ሙሉ፡ በሙሉ፡ የፈረንሳይ፡ ጦር፡ አካዳሚ፡ ትምህርት፡ መርሐ፡ ግብር፡ ነው። ወቅቱ፡ አስቸኳይ፡ ስለ፡ ሆነ፣ የሦስቱን፡ ዓመት፡ የጦር፡ ትምህርት፡ መርሐ፡ ግብር፣ ዓመት፡ ተመንፈቅ፡ ባልሞላ፡ ጊዜ፣ አንደኛ፡ በመውጣት፡ አጠናቀው፣ በመድፈኛ፡ ደንብ፡ ውስጥ፣

ኅዳር፡ 14፡ ቀን፡ 1928፡ ዓ.ም.፣ የመቶ፡ አለቃ፤

ታኅሣሥ፡ 14፡ ቀን፡ 1928፡ ዓ.ም፣ የሻምበል፤

ጥር፡ 21፡ ቀን፡ 1928፡ ዓ.ም.፣ የሻለቃ፡ (የ5፡ ሻምበል፡ አዛዥ)፤

በመጨረሻም፣ የካቲት፡ 21፡ ቀን፡ 1928፡ ዓ.ም.፣ በሊየተና፡ ኮሎኔልነት፡ ማዕርግ፣ አዲስ፡ ለተቋቋመው፡ ብሪጌድ፡ ዋና፡ ኤታ፡ ማዦር፡ ሹም፡ ሆነው፡ በንጉሠ፡ ነገሥቱ፡ ተሠየሙ።

አገልግሎት
ወዲያው፣ ሚያዝያ፡ 13፡ ቀን፡ 1928፡ ዓ.ም.፣ አዲሱን፡ ጦር፡ በኤታ፡ ማዦር፡ ሹምነት፡ በጣርማ፡ በር፡ ግንባር፡ አዘመቱ። የኢትዮጵያ፡ ጦር፡ ከተፈታ፡ በኋላ፣ ጥቂት፡ የገነት፡ መኰንኖችንና፡ ሰራዊቱን፡ ይዘው፣ ሚያዝያ፡ 24፡ ቀን፡ 1928፡ ዓ.ም.፡ አርበኝነት፡ ወጡ። እስካ 1930፡ ዓ.ም.፡ ፍጻሜ፡ ድረስ፣ ለሁለት፡ ዓመት፡ ተኩል፣

ሸዋ፡ (አዲስ፡ አበባ፡ ዙሪያ፣ ሙሎ፣ ሰላሌ፣ ተጕለት፣ መርሐቤቴ፣ ግንደበረት፣ ጊዳ፣ ሜጫ፣ ሜታ፣ …)፤

ወለጋ፡ (አሞሩ፣ ኤበንቱ፣ ጨልያ፣ ሆሮ፣ ጉድሩ፣ …)፣

ጎጃም፡ (አለፋ፡ ጣቁሳ፣ ቡሬ፣ አሰዋ፡ ጉደራ፣ አገው፡ ምድር፣ ማቻከል፣ …)

ከደጃዝማች፡ ዘውዴ፡ አስፋው፡ ዳርጌ፣ ከራስ፡ አበበ፡ አረጋይና፣ ከታላላቅ፣ ያርበኝነት መሪዎች፡ ጋራ፡ በጦር፡ መሪነት፣ እዚህ፡ ሊዘረዘሩ፡ በማይችሉ፡ ልዩ፡ ልዩ፡ ውጊያዎች፡ በታላቅ፡ ጀግንነት፡ ተዋግተውና፡ አዋግተው፣ ባርበኞች፡ ዘንድ፡ የላቀ፡ ዝናን፣ የተለየ፡ አድናቆትን፡ አትርፈዋል።

በወቅቱ፣ ሱዳንን፡ በቅኝ፡ ግዛትነት፡ ይገዛ፡ የነበረው፡ የብሪታንያ፡ መንግሥት፣ ኢትዮጵያን፡ ለኢጣሊያ፡ አፅድቆ፡ ኖሮ፣ መስከረም፡ 19፡ ቀን፡ 1931፡ ዓ.ም.፣ ሊ.፡ ኮሎኔል፡ ነጋ፡ ኀይል፡ ሥላሴ፡ ከተከተሏቸው፡ ዐርበኞች፡ ጋራ፣ የሱዳንን፡ ጠረፍ፡ እንዳለፉ፣ ጠረፉን፡ የሚጠብቀው፡ የብሪታንያ፡ ጦር፡ ይይዛቸዋል። ጥቂት፡ ወራት፡ በጦር፡ እስረኝነት፡ ገዳሬፍና፡ ካርቱም፡ እንደ፡ ቈዩ፣ ኢጣልያ፡ በታላቋ፡ ብሪታንያ፡ ላይ፡ ጦርነት፡ በማወጇ፣ የታሰሩት፡ ዐርበኞች፡ ተፈቱ።

ሊ.፡ ኮሎኔል፡ ነጋ፡ ኀይል፡ ሥላሴም፣ ከሰራዊቱ የተላኩትን፡ መልክት፡ (ያርበኝነት፡ ተጋድሎው፡ የደረሰበትን፡ ደረጃ፣ ያስገኛቸውንም፡ ውጤቶች፡ አስታውቆና፣ ከንጉሠ ነገሥቱ፡ ጋራ፡ ግንኙነትን፡ መሥርቶ፣ የጦር፡ መሣሪያና፡ የሥንቅ፡ ርዳታ፡ በቶሎ፡ ላርበኛው፡ እንዲደርስ እንዲያደርጉ የሚጠይቀውን ደብዳቤ) በብሪታንያ፡ ባለሥልጣኖች፡ በኩል፡ ለንጉሠ፡ ነገሥቱ፡ አስተላልፈው፣ ወደ፡ ኢትዮጵያ፡ ለመመለስ፣ ዐብረዋቸው፡ የሚዘምቱ፡ ሁለት ሺህ፡ የሚኾኑ፡ ስደተኞችን፡ ላርበኝነት፡ አሰባስበው፡ በሚያደራጁበት፡ ጊዜ፣ የታላቋ፡ ብሪታንያ፡ መንግሥት፡ በጎ፡ ፈቃድና፡ ወታደራዊ፡ ድጋፍ፡ ደረሰላቸው።

ሰኔ፡ 27፡ ቀን፡ 1932፡ ዓ.ም.፡ ንጉሠ፡ ነገሥቱ፡ ከብሪታንያ፡ ወደ፡ ካርቱም፡ እንደ፡ ተመለሱ፣ ሊ.፡ ኮሎኔል፡ ነጋ፡ ኀይለ፡ ሥላሴን፡ አስጠርተው፣ ሶባ፡ እተባለው፡ የሱዳን፡ ቀበሌ፣ አዲስ፡ የሚቋቋመውን፡ ቅዱስ፡ ጊዮርጊስ፡ የጦር፡ ትምህርት፡ ቤት፡ ከብሪታንያ፡ ጦር፡ መኰንኖች፡ ጋራ፡ በጣምራ፡ እንዲመሩ፡ አዘዟቸው።

በወቅቱ፡ የመርድ፡ አዝማች፡ አስፋ፡ ወሰን፡ ኀይለ፡ ሥላሴ፡ ወታደራዊ፡ ማዕረግ፡ የሻለቃ፡ ስለ፡ ነበር፣ ከርሳቸው፡ ማዕርግ፡ በልጦ፡ እንዳይገኝ፣ ሊ.፡ ኮሎኔል፡ ነጋ፡ ኀይለ፡ ሥላሴ፣ ማዕርጋቸው፡ አንድ፡ ደረጃ፡ ዝቅ፡ ብሎ፣ በሻለቅነት፡ ማዕርግ፡ ሥራቸውን፡ እንዲቀጥሉ፡ ከንጉሠ፡ ነገሥቱ፡ ታዘዙ። ኮሎኔሉም፣ ጃንሆይ፤ ጉዳዬ፡ ከሥራው፡ እንጂ፡ ከማዕረጉ፡ አይደለም፤ ብለው፡ ተቀበሉ።

የካቲት፡ 1933፡ ዓ.ም.፡ ኢትዮጵያ፡ ገብተው፣ ከ3፡ ወር፡ ዘመቻ፡ በኃላ፣ ደብረ፡ ማርቆስ፡ ከኢጣሊያ፡ ጦር፡ እጅ፡ ነጻ፡ ወጣች። ሻለቃ፡ ነጋ፡ ኀይለ፡ ሥላሴ፣ በጦሩ፡ በኩል፡ ለሚኖረው፡ ጉዳይ፡ ኹሉ፡ ኀላፊ፡ ኾነው፣ የንጉሠ፡ ነገሥቱንም፡ ወታደራዊ፡ መመሪያ፡ ይዘው፣ ከምክትሎቻቸው፡ ከሻለቃ፡ ዐቢይ፡ አበበና፡ ከሻለቃ፡ ሙሉጌታ፡ ቡሊ፡ ጋራ፣ የንጉሠ፡ ነገሥቱን፡ ባለሙሉ፡ ሥልጣን፡ እንደራሴ፡ ቢትወደድ፡ መኰንን፡ እንዳልካቸውን፡ ዐጅበው፣ ሚያዝያ፡ 5፡ ቀን፡ 1933፡ ዓ.ም.፡ በማለዳ፡ ከደብረ፡ ማርቆስ፡ ባየርዠበብ፡ (አይሮፕላን)፡ ተጉዘው፣ የኢትዮጵያ፡ መናገሻ፡ ከተማ፣ አዲስ፡ አበባ፣ ጧቱኑ፡ ገቡ። ሻለቃ፡ ነጋ፡ ኀይለ፡ ሥላሴን፡ ካርበኝነት፡ ዘመን፡ አንሥቶ፡ ያውቋቸውና፡ ያደንቋቸው፡ የነበሩት፣ ዝነኛዋ፡ ባለቅኔ፡ ንጋቷ፡ ከልካይ፣ የምሥራቹን፡ እንደ፡ ሰሙ፣

ጠቅል፡ ባንዲራውን፡ ጠረፍ፡ ቢዘረጋ፣

አዲስ፡ አበባ፡ ላይ፡ አስቀድሞ፡ ነጋ።

ሲሉ፡ ገጠሙላቸው።

አዲስ፡ አበባ፡ እንደ፡ ገቡም፣ ጽሕፈት፡ ቤታቸውን፡ በጃንሆይ፡ ዐፄ፡ ምኒልክ፡ ቤተ፡ መንግሥት፡ ግቢ፡ ውስጥ፡ አድርገው፣ ያርበኛውን፡ ጦር፡ በከተማዋ፡ ዙሪያ፡ አዋቅሮ፡ በማሰምራትና፣ ከብሪታንያ፡ ጦር፡ ኀላፊዎች፡ ጋራ፡ ዐብሮ፡ በመሥራት፣ የከተማውን፡ ጠቅላላ፡ ጸጥታ፡ አረጋግጠው፣ ወታደራዊ፡ አስተዳደሩን፡ አደራጅተው፣ ንጉሠ፡ ነገሥታቸውን፡ በመናገሻ፡ ከተማዋ፡ ለመቀበል፡ አስፈላጊውን፡ ዝግጅትና፡ መስተንግዶ፡ አከናወኑ። በዚህ፡ ሥራቸው፣ ከብሪታንያ፡ ጦር፡ አመራር፡ ጋራ፣ አልፎ፡ አልፎ፣ አለመግባባትና፡ ግጭት፡ ቢፈጠርም፡ ቅሉ፣ ሻለቃ፡ ነጋ፡ ኀይለ፡ ሥላሴ፣ አንዳችም፡ ጊዜ፡ ቢኾን፡ የኢትዮጵያን፡ እግዚእና (ሉአላዊነት)፡ ሳያስደፍሩ፣ ክብሯንም፡ ሳያስነኩ፣ ተልእኳቸውን፡ ጠንቅቀው፡ ፈጽመዋል።

ሰኔ፡ 7፡ ቀን፡ 1954፡ ዓ.ም፣ የሊዬተና፡ ዤኔራልነት፡ (ታኅሣሥ፡ 11፡ ቀን፡ 1951፡ ዓ.ም.፣ የሜጀር፡ ዤኔራልነት፡ ማዕረግ) ተሰጥቷቸው ወደ ጎንደር፡ ሄዱ። ጎንደር እንደ፡ ገቡም፤

“አህያ፡ መጣች፡ ተጭና፡ ሞፈር፤

በነጋ፡ ጊዜ፣ እኽል፡ እንዳፈር።”

በሚል፡ ትንቢታዊ፡ ቃል፡ ሕዝቡ፡ ተቀበላቸው።

ወደ ሲዳሞ ተሹመው በሄዱበትም ጊዜ ልክ እንደ ጎንደሩ ሁሉ፤

በባሌ፡ ዑጋዴ፣ በጎንደር፡ አስመራ፣

እየነጋ፡ ሲኼድ፣ ሥራው፡ እያበራ፣

በየደረሰበት፡ ሀገሩን፡ ሲያኰራ፣

ዕድል፡ ሲያጋጥመው፡ እንዲሁ፡ በተራ፣

ብቅ፡ አለ፡ በደቡብ፡ ለሲዳሞ፡ ጮራ።

ሲሉ፡ ተቀኝተውላቸዋል።

ሊ.፡ ዤኔራል፡ ነጋ፡ ኀይለ፡ ሥላሴ፡ በ1953፡ ዓ.ም.፡ በመከላከያ፡ ሚኒስቴር፡ ሚኒስትር፡ ዴታ፡ በነበሩበት፡ ወቅት፣ ስላርበኝነት፡ የአምስት፡ ዓመት፡ ታሪክ፡ ለቀረበላቸው፡ ጥያቄ፣ ያሰናዱትናቀ ከ50 አመት በኋላ ለ70ኛው የድል በአል መታሰቢያን ምክንያት በማድረግ፣”የ1928—1933፡ ዓ.ም.፡ ዐርበኝነት፤ እንዴት፡ እንደተወጠነና፡ እንደተስፋፋ፡ የሚገልጥ።” በሚል ርእስ ለህትመት የበቃውን ባለ 12 ገጽ ጽሑፋቸውን መመልከት እጅግ ጠቃሚ ይሆናል። (ለተጨማሪ በወሌ፡ ነጋ የተዘጋጀውና የ1928-1933፡ ዓ.ም፡ ዐርበኝነት፤ እንዴት፡ እንደተወጠነና፡ እንደተስፋፋ፡ የሚገልጥ። (ሚያዝያ፡ 27፡ ቀን፣ 2003፡ ዓ.ም)” በሚል ርእስ ”የሚያዝያ፡ 27፡ ድል፡ በዓል፡ መታሰቢያ” ይሆን ዘንድ ለንባብ የበቃው ስራቸውን ማየት ተገቢ ነው።)

የድርስት ሕይወታቸው
ከስራዎቻቸው እጅግ፡ ጥቂቶቹ፡ ብቻ፡ ለህትመት የበቁላቸው ሲሆን፣ ስለ፡ ታሪክም፡ ኾነ፡ ስለግዛት፡ ፍልስፍና፣ ስለ፡ ቀለምም፡ ኾነ፡ ስለ፡ ቋንቋ፣ ዐያሌ፡ ጽሑፎችን፡ ደርሰዋል። ተጽፈው፡ የተዘጋጁና ያለቀላቸው፤ ነገር፡ ግን፡ ገና፡ ያልታተሙ፡ ሌሎች፡ በርካታ መጽሐፎችም፡ አሏቸው። ያገር፡ ፍቅር፡ መዝሙሮችም የስራዎቻቸው አካል ነበሩ።

ማህበራትን ከማቋቋም እስከ መምራት

አገር አቀፍና የልማት ማኅበራትን፣ ድርጅቶችን፡ … አቋቁመዋል፤ ብዙዎቹንም፡ በሊቀ፡ መንበርነት፡ መርተዋል። ጥቂቶቹም፤

ጥንታዊት፡ ኢትዮጵያ፡ ሀገራዊ፡ የዠግኖች፡ ማኅበር፡ (ሚያዝያ፡ 1956፡ ዓ.ም.)፣ ሊቀ፡ መንበር፤ የይፋት፡ ልማት፡ ሕዝባዊ፡ ኅብረት፡ (ግንቦት፡ 10፡ 1960፡ ዓ.ም.)፣ ሊቀ፡ መንበር፤ የኢትዮጵያዊያን፡ ሀገራዊ፡ ሥልጡንሕዝባዊ፡ አንድነት፣ ሐምሌ፡ 1፡ ቀን፡ 1967፡ ዓ.ም.፣ ሊቀ፡ መንበር፤ (ሚያዝያ፡ 10፡ 1982፡ ዓ.ም.)፡ የጊዜያዊ፡ ከዋኝ፡ ምክር፡ ሊቀ፡ መንበር፤ የኢትዮጵያ፡ ዐውደ፡ ቀለም፡ (መስከረም፡ 24፡ ቀን፡ 1990፡ ዓ.ም.)፣ ሊቀ፡ መንበር። በ1954፡ ዓ.ም.፣ የኢትዮጵያ፡ እግር፡ ኳስ፡ ፌደሬሽን፡ ሊቀ፡ መንበር፡ በነበሩበት፡ ወቅት፣ ኢትዮጵያ፡ የአፍርካ፡ ዋንጫን፡ ለመጃመሪያ፡ ጊዜ፡ አሸንፋለች። በብፁዕ፡ ወቅዱስ፡ አቡነ፡ ባስልዮስ፡ ርእሰ፡ ሊቃነ፡ ጳጳሳት፡ ወፓትረያርክ፡ ዘኢትዮጵያ፡ ሠያሚነት፣ የኢትዮጵያ፡ ኦርቶዶክስ፡ ተዋሕዶ፡ ቤተ፡ ክርስቲያን፡ ሥጋዊ፡ አስተዳደር፡ ጉባኤ፡ አባል፡ ኾነው፡ ለጥቂት፡ ዓመት፡ አገልግለዋል። በሌሎች በርካቶችም እንዲሁ። አምባሳደርም ነበሩ።

ሽልማቶች

ከኢትዮጵያ፡ ንጉሠ፡ ነገሥት፡ መንግሥት፤

•ያርበኝነት፡ ሜዳይ፣ ጥር፡ 12፡ ቀን፡ 1937፡ ዓ.ም፤

•የቅዱስ፡ ጊዮርጊስ፡ የጦር፡ ሜዳ፡ ሜዳይ፣ ጥር፡ 12፡ ቀን፡ 1937፡ ዓ.ም፤

•የዳግማዊ፡ ምኒልክ፡ የመኰንን፡ ደረጃ፡ ሊሻን፣ መጋቢት፡ 12፡ ቀን፡ 1943፡ ዓ.ም፤

•የኢትዮጵያ፡ የክብር፡ ኮከብ፡ ታላቅ፡ መኰንን፣ ሚያዝያ፡ 27፡ ቀን፡ 1943፡ ዓ.ም፤

•የድል፡ ኮከብ፡ ሜዳይ፣ ሚያዝያ፡ 16፡ ቀን፡ 1948፡ ዓ.ም፤

•የዳግማዊ፡ ምኒልክ፡ ኮርዶን፡ ኒሻን፣ ሚያዝያ፡ 27፡ ቀን፡ 1958፡ ዓ.ም።

የውጭ፡ መንግሥታት፡ ከሸለሟቸው፡ ውስጥ፤

•ከስዊድን፡ መንግሥት፣ Kömmendor med stora av Kungl. Svärdsorden፥

የካቲት፡ 1952፡ ዓ.ም፤

•ከታላቋ፡ ብሪታንያ፡ መንግሥት፣ Knight Com­mander of the Victoria Order፤ 1957፡ ዓ.ም.፤ ይገኙባቸዋል።

ከባለቤታቸው፡ ከክብርት፡ ወይዘሮ፡ ከፈይ፡ ኀይለ፡ ሥላሴ፡ ሰባት፡ ልጆች፡ ወልደዋል፤ ሦስት፡ የልጅ፡ ልጆችንም፡ አይተዋል።

ሊ.ጄኔራል፡ ነጋ፡ ኀይለ፡ ሥላሴ፣ እንግሊዝ፡ አገር፡ 32፡ ዓመት፡ በስደት፡ ከቈዩ፡ በዃላ፣ ሚያዝያ፡ 8፡ ቀን፡ 1999፡ ዓ.ም.፡ ከባለቤታቸው፡ ጋራ፡ ወደ፡ ውድ፡ አገራቸው፡ ኢትዮጵያ፡ ተመልሰው፣ ዓመት፡ ከሦስት፡ ወር፡ አዲስ አበባ ተቀምጠዋል። ሐምሌ፡ 15፡ ለ16፡ አጥቢያ፡ 2000፡ ዓ.ም.፡ ዐርፈዋል።

የክቡር፡ ሊ.፡ ዤኔራል፡ ነጋ፡ ኀይለ፡ ሥላሴ፡ ቀብር፡ ሥርዐት፥ ሐምሌ፡ 19፡ ቀን፡ 2000፡ ዓ.ም፣ ዐዲሰ፡ አበባ፡ እመንበረ፡ ጸባኦት፡ ቅድስት፡ ሥላሴ፡ ቤተ፡ ክርስቲያን፣ ቤተ፡ ሰብ፡ ቤተ፡ ዘመድ፣ ወዳጅ፡ ወገን፣ ብዙ፡ ሕዝብ፡ በተገኘበት፣ ባርበኞች፡ ዐጀብ፣ በተዋሕዶ፡ ክርስቲያን፡ ሥርዐት፡ ተፈጽሟል።

ስም ከመቃብር በላይ ነው።

08/25/2023

ፒተር አብረሃምስ: አፓርታይድን የታገለው ትውልደ ኢትዮጵያዊ
=====
በስደት ወደ ደቡብ አፍሪካ ሄደው ከነበሩት ኢትዮጵያዊ አባቱ ፒተር ሄንሪ (Peter Henry Abrahams Deras) እና ከፈረንሳዊ/አፍሪካዊት እናቱ የተወለደው ፒተር የትውልድ ስፍራው እዛው ደቡብ አፍሪካ፣ ጆሀንስፐርግ አካባቢ (Vrededorp የምትባል ስፍራ) ሲሆን፣ ኢትዮጵያዊ አባቱን በሞት የተነጠቀው ገና በልጅነቱ ነበር።

በሀገሪቱ ውስጥ 21 በመቶ የሆኑ (የደቡብ አፍሪካ ነጭ ሰፋሪዎች ነው የሚባሉት)፣ የፖለቲካ እና ኢኮኖሚያዊ ስልጣንን በመያዝ የአገሩን ባለቤት ሲጨቁኑ የኖሩበት፤ ዜጎች በገዛ አገራቸው ሰጨቆኑ የኖሩበት የነበረ መሆኑ ለፒተር አብረሃስ የብዕር ተጋድሎ (በ1910 የተመሰረተው የደቡብ አፍሪካ ኅብረት፤ የምልክት መሪው ኔልሰን ማንዴላ መሆናቸው እንዳለ ሆኖ) መቀስቀስ ምክንያት እንደ ነበር ይታወቃል። በመሆኑም አጠቃላይ ሥነጽሑፋዊ ምርቱ መዕከላዊ (ዐቢይ) ጭብጥ ይህንኑ አስከፊ ስርአት ማውገዝ ብቻ ሳይሆን ማህበረሰቡን በማንቃት፣ ፍትህና ርትእን በመስበክ … በስርአቱ ላይ እንዲነሳና እንዲወገድ ሲያደርጉ ፀረ-አፓርታይድ ታጋዮች መካከል ከቆዩት አንዱ ነበር።

”የ20ኛው ክፍለ ዘመን እውቅ ጸሐፊና ጋዜጠኛ” መሆኑ የተመሰከረለት ፒተር አብረሃምስ የተለያየ ዜግነት ካላቸው ወላጆቹ መወለዱ ለበኋላ ማንነቱ፣ ለፀረ-ቅኝ አገዛዝ ትግሉና ፀረ-አፓርታይድ አቋሙ መሰረት (mulatto background) እንደሆነው ይነገራል።

የእነ ሄንድሪክ ቨርዎርድ (ከ1958-66 የብሔራዊ ፓርቲ መሪ ሆኖ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበረ እና የአፓርታይድ ፖሊሲን ተግባራዊ ለማድረግ ቁልፍ ሚና የነበረው) ማስፈራሪያ እንኳን ያልበገረው ፒተር በሃያኛው ክፍለ ዘመን በደቡብ አፍሪካ ለተስፋፋውና ለየት ያለ የዘር-ሶሻል ርዕዮተ ዓለምን ለሚያራምደው አፓርታይድ ያለው ጥላቻ በስሜት ሳይሆን በምክንያት ላይ የተመሰረተ በመሆኑ፣ በስራዎቹ በብዙዎች ከጀፍተኛ አድናቆትን የያተረፈ ሲሆን፤ ለዚህም ከሁሉም ቀዳሚ ተጠቃሽና ተፅእኖ ፈጣሪ (seminal novel) በሆነው በMine Boy (1946) ስራው ውስጥ የሚያራምደው ሰውን መሰረት ያደረገ አስተሳሰቡና ሁሉም ጨቋኙም ተጨቋኙም ራሱን እንዲያይ ያደረገበት አቀራረቡ ነው።

ስፔንሰር ክዊን (ከላይ ይመልከቱ) ”A Wreath for Udomo”ም እንዲሁ በ2ኛነት ደረጃ ታዋቂና ተወዳጅ ስራው መሆኑ ተመስክሮለታል። በተለይ ስራዎቹ ዘረኝነትን፣ ፖለቲካን ….. (የደቡብ አፍሪካ ሥነፅሁፍ አቢይ ጭብጡ racial segregation and political and economic discrimination against non­whites መሆኑን ያስታውሷል) የሚያብጠለጥሉና የሚያጋልጡ እንደ መሆናቸው መጠን የመላው ደቡብ አፍሪካዊያን ድምፅ ሆነው እስከ ማገልገል መዝለቃቸው ይታወቃል።

በዚህ ተወዳጅና አብዝቶም ተጠቃኝ ስራው ጥቁር (ወይም ባንቱ)፣ ቀለም (የተቀላቀለ)፣ ህንድ እና ነጭ ሰሜን አፍሪካውያን … ልዩነት የነበረውን ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ስርአት/ልዩነት ያስከተለውን አፓርታይድ በምክንያት አጋልጧል፣ ተችቷል፤ ”መቀጠል የሌለበት” መሆኑን አስቀምጧል፤ ሊወገድ ይገባዋል” ሲልም እቅጩን ተናግሯል።

ይህ፣ በ1900ዎቹ፣ ከቦር ጦርነት በኋላ በደቡብ አፍሪካ የተጀመረውን የዘር ልዩነት አንድ በአንድ እየቆጠረ በማጋለጥ የተሳካለት ፒተር በአንድ ወይም በሁለት ስራዎች የተገደበ፤ በርካታ (ወንጀል፣ ፖለቲካ፣ ፀረ-አፓርታይድ …) መጻሕፍትን ለንባብ ያበቃ ብርቱ ሰው ብቻ ሳይሆን፤ ያለ መቋረጥ በጋዜጦች ላይ በሚያወጣቸው ጽሑፎቹም ታዋቂነትን አትርፏል።

አፓርታይድን ከስሩ ፈንግሎ ለመጣል የራሱን የማይተካ ድርሻ ተወጥቷል።

ባልተቋረጠ ሁኔታ ሥነፅሁፋዊ ምርቶቹን ለአለም ሲያበረክት የቆየው ፒተር፣ በአሁኑ ሰአት ሳይቀር፣ ከአማዞን ጀምሮ የአለምን የመጽሑፍት ገበያ የተቆጣጠሩት ስራዎች በርካቶች ሲሆኑ፤

Oblivion, The Tutor, The Fury of Rachel Monette, Hard Rain, The Fan, Crying Wolf, The Right Side (በSpencer Quinn ብእር ስሙ የፃፈው), the Echo Falls Mys­teries for children, … ጥቂቶቹ ናቸው።

‘አፍሪካንስ’ ቋንቋ በትምህርት ቤት ውስጥ ጥቅም ላይ መዋሉን ከተቃወሙ ጥቁር ተማሪዎች ውስጥ አንዱ የሆነው፤ እአአ በ1976 በስዌቶ በተካሄደ ዐመፅ ወቅት በፖሊስ እጅ በተገደለው የ12 አመት ታዳጊ ሄክተር ፒተርሰን የተሰየመውና የፀረ-አፓርታይድ ትግል ወቅት የነበሩ ቁልፍ ክንዋኔዎችን የሚያወሳው ሙዚየም የዘመነ አፓርታይድን ግፍና ዘረኛ ማንነት ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ መሆኑን መዛግብት ይመሰክራሉ። ይህ ሙዚየም ካካተታቸው ታሪኮች መካከል የፒተር አብረሃምስ ስራዎች ጥቂቶቹ ናቸው።

ይህ ሙዚየም በከፍተኛ ባለስልጣናት ሳይቀር የሚጎበኝ ሲሆን፤ በቅርቡ የአሜሪካው ብሊንከን ደቡብ አፍሪካን ከሩሲያና ቻይና ነጥለው ወደ ራሳቸው ለማምጣት (ባይሳካም) ባደረጉት ጉዞ እንዲጎበኙ የተጋበዙት ይህንኑ ሙዚየም ሲሆን፤ በወቅቱም “የሄክቶር ታሪክ ጎልቶ የሚሰማን ነው ምክንያቱም እኛም ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ የራሳችን የነፃነት እና እኩልነት ትግል አለን። የደቡብ አፍሪካ ታሪክ ልዩ ነው ነገር ግን ደግሞ በጥልቅ ጎልቶ እንዲሰማ የሚያደርግ በርካታ ተመሳሳይ ነገሮችም አሉን።” ማለታቸው ተዘግቧል።

እንደነ ማንዴላ (ንጉስ ኃይለ ሥላሴ ለማንዴላ ሽጉጥ መሸለማቸውን፣ ሽጉጡም ደቡብ አፍሪካ ብሄራዊ ሙዚየም የሚገኝ መሆኑን ልብ ይሏል)፣ ደቡብ አፍሪካ በተለይም በፀረ-አፓርታይድ ትግል መሪነታቸው የሚታወቁት ዴዝሞን ቱቱ፤ አልበርት ሉቱሊ፣ ዎልተር ሲሱሉ እና የመሰሉት የቀድሞ የኤኤንሲ አባላት ሁሉ፤ ከአፓርታይድ ነፃ የሆነች ደቡብ አፍሪካን በመፍጠሩ እንቅስቃሴ ውስጥ በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሰው ፒተር አብረሃምስ የቀለም ልዩነትና የነጮች የበላይነት እንዲያከትም ሌት ተቀን የሰራ፤ ያለ ፍርሀትም የተጋፈጠ፤ ኢ-ፍትሃዊነትን፣ የጎሳ ዘረኝነትን በአገር ውስጥም ሆነ በመላው ዓለም የታገለ የብዕር ጀግና ነው።

በዘመነ አፓርታይድ ምን ምን ተግባራት ተፈፅመው ነበር፣ ፒተርንም ሆነ ሌሎች ደራሲያንን ለዚህ (ለAnti-Apartheid Movement) ያበቃቸው ምንድን ነው? ብሎ ለጠየቀ ምላሹ፤

… የዘር ጋብቻ በወንጀል ተፈርዶበታል። … ጥቁሮች ደቡብ አፍሪካዊያን ንብረት ሊኖራቸው አልቻለም። … ትምህርት በቀለም (በነጭና ነጥቁር) ተለያይቷል። … በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ ሰዎች በዘር ተከፋፍለዋል። … የአፍሪካ ብሄራዊ ኮንግረስ ፓርቲ እንዳይንቀሳቀስ ታግዷል። ንብረት (መሬትን ጨምሮ) በጥቂት ነጮች መዳፍ ስር ወድቋል። ወዘተርፈ …. (ለተጨማሪ ”Writ­ing South Africa Literature, Apartheid, and Democracy, 1970–1995” መመልከት ጠቃሚ ነው።)

የሚል ሲሆን፤ የብዕር አለቆቹን፣ እነ ፒተር፣ አሌክስ ላጉማና የመሳሰሉትን ወደዚህ አይነቱ የብዕር ተቃውሞ ያስገባቸውም ይሄው ነው። (ወደ እኛም አገር ስንመጣ የሥነጽሑፍ ስራዎቻችን ዘመናቸውን ነው የሚመስሉት። አሁን አሁን ግራ አጋቢ ሆኑ እንጂ፣ ለምሳሌ በጣሊያን ወረራ ጊዜ የተሰሩትን ማየት ይቻላል።)

ምንም እንኳን አንዳንድ በወቅቱ፣ በመጨረሻው ሰአት የተፃፉ ሰነዶች ”በደቡብ አፍሪካ የነበረው የአፓርታይድ ስርዓት እ.ኤ.አ. በ1990 እና 1993 ተከታታይ ድርድሮች እና በዲ ክለርክ መንግስት በአንድ ወገን እርምጃዎች ተጠናቀቀ።” ይበሉ እንጂ፣ አፓርታይድን ገዝግዘው የጣሉት ብዕረኞች መሆናቸው የታወቀ ነው። ይህንን ለማረጋገጥ ደግሞ ከብዙዎቹ አንዱና ቀዳሚ የሆነውን፣ የፒተር አብረሃምስን ስራዎች መመልከቱ በቂ ማሳያ ይሆናል።

ወደ ማጠቃለያችን ከመሄዳችን በፊት የአፍሪካን ሥነፅሁፍ ልዩ መገለጫ እንመልከት፤ ከዛ ውስጭም የደቡብ አፍሪካን ድርሻ እንይ።

የደቡብ አፍሪካ ደራሲያን ስንል ፀረ አፓርታይድ ትግል የሚያካሂዱና ከየትኛውም አይነት ቀለም (ዘር) የሆኑትን ሲሆን፤ ተወላጆቹ (South African Black Authors የሚሏቸው)ም አሉ። እንደውም፣ እንደሚጠበቀውም፣ አብዛኞቹም እነዚሁ ተወላጆች ሲሆኑ፤ ከእነዚህ ውስጥም፣ ልክ እንደ ፒተር አብርሃምስ ሁሉ፣ ግንባር ቀደሞች (Sol Plaatje, Zakes Mda, Kopano Matl­wa, Zukiswa Wanner, Pumla Gqola እና ሌሎችም) አሉ። (በአፍሪካ ሥነፅሁፍ ውስጥ የቹና አቼቤን Things Fall Apart የ1ኛነት ስፍራን ልብ ይሏል።)

በ19ኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃ ላይ ህልውናውን ያረጋገጠውና በ20ኛው ክፍለ ዘመን ከፍተኛ መሻሻልን ያሳየው በደቡብ አፍሪካ ሥነፅሁፍ ውስጥ በአቢይ ርእስነት ትኩረት የሚደረግባቸው ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ስነልቦናዊ፣ ባህላዊ … ጉዳዮች ሲሆኑ፤ እነሱም እራሱ አፓርታይድን ጨምሮ እሱ ያስከተላቸውን መዘዞች ሁሉ (Apartheid, Negritude, As­similation, Racism, lack of education, dual identity of the mixed people etc) ናቸው።

እንደ አጠቃላይ የአፍሪካ ሥነጽሑፍ አቢይ ትኩረት ማህበራዊ (በተለይም ባህል ላይ)፣ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ሲሆን እነዚህ በተን ተደርገው ሲታዩ ደግሞ በርካታ (slave narratives, protests against colonization, calls for independence, African pride, hope for the future, and dissent) ናቸው። ይህ የጋራ ባህርይና ልዩ ትኩረት አሰጣጥ ዝም ብሎ በአጋጣሚ የሆነ ሳይሆን፤ የጋራ ጠላት የሆነው ቅኝ አገዛዝ ያመጣው የጋራ ስሜት፣ የጋራ አቋም፣ የጋራ አስተሳሰብና የጋራ መፍትሄ ፍለጋ ነው። የደቡብ አፍሪካ ሥነጽሑፍም ይህንኑ የሚጋራ ሲሆን፣ የዛሬው የአምዳችን ”እንግዳ”ም ሆነ፣ የገጣሚ ሎሬት Keorapetse William Kgositsile (South Africa’s National Poet Laure­ate) ስራዎች ከዚሁ የተቀዱ እንደ መሆናቸው መጠን ይህንኑ ሲያስተጋቡ እንመለከታለን።

በመጨረሻም፣ በ97 አመት (3 ማርች 1919 – 18 ጃንዋሪ 2017) እድሜው ከዚህ አለም በሞት የተለየው የዛሬው የባለውለታችን አምድ ተስተናጋጅ፣ ፒተር አንረሃምስ ለተወለደባት አገሩ ደቡብ አፍሪካ ብቻ ሳይሆን የነጭ የበላይነትን በመቃወምና የርትእና ፍትህን አስፈላጊና አይቀሬነት፤ ስለ ዲሞክራሲ፣ እኩልነትና ነፃነት በማስተማር እድሜውን አሳልፏል። እንደ ማንኛውም ትውልደ ኢትዮጵያዊ አገሩን (ኢትዮጵያን)ም በስራዎቹና በእሱ ጠንካራ ማንነት አማካኝነት አስጠርቷል። በመሆኑም፣ ደቡብ አፍሪካዊያን ብቻ ሳይሆኑ፤ መላው ጥቁር ህዝብ ብቻ ሳይሆን፣ መላው የፍትህና ርትእ ደጋፊ፤ አፍቃሬ ዲሞክራሲና አቀንቃኝ ሁሌም ሲያነሳው ይኖራል። በተለይ የነጮቹን ሴራና ራስ ወዳድነትን መሰረት ያደረገ ስግብግብነት፤ ኢፍትሀዊነት የሚያውቅ ሁሌም ከፒተር አብረሀምስ ጋር እንደሚሆን አያጠራጥርም።

https://am.sewasew.com/p/ፒተር-አብረሃምስ-አፓርታይድን-የታገለው-ትውልደ-ኢትዮጵያዊ

08/16/2023

ታሪካዊቷን መርጡለ ማርያም ገዳም ርዕሰ ርዑሳን ተብለው እየተሾሙ ያገለገሉ አስተዳዳሪዎች ዝርዝር።
======
ጥንታዊት እና ታሪካዊት ርዕሰ አድባራት ወገዳማት መርጡለ ማርያም ገዳም በአማራ ዝሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በምሥራቅ ጎጃም ዞን አስተዳደር በእነብሴ ሳርምድር ወረዳ ናዕሰ ከተማ ትገኛለች። በሀገራችን ኢትዮጵያ ዋና ከተማ አዲስ አበባ በ364 ኪሎ ሜትር፣ ከክልሉ ዋና ከተማ ባህር ዳር በ180 ኪሎ ሜትር፣ ከምሥራቅ ጎጃም ዞን ዋና ከተማ ደብረ ማርቆስ በ192 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኝ ጥንታዊትና ታሪካዊት ገዳም ናት ።

ይህች ታሪካዊት ገዳም ከላይ እንደገለጽነው ከአዲስ አበባ በስተሰሜን የዐባይ ወንዝን ተሳግሮ የደጀን ከተማን አቋርጦ የብቸናን እና የደብረ ወርቅን ከተማ አልፎ ጉንደወይን ከተማ ሲደርስ ወደ ቀኝ ማለትም ወደቀኝ በመታጠፍ ወደ ፀሐይ መውጫ /ምሥራቅ/ ቢጓዙ በ27 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ጥንታዊትና ታሪካዊት መርጡለ ማርያም ገዳም በአገር በቀል አፀዶች እና እድሜ ጠገብ ዛፎች አሸብርቃና ተውባ ዙሪያዋን በሚፍለቀለቁ መንደሮች ታጅባ ከባህር መካከል ያለች ደሴት መስላ ትታያለች ።

ይህችው ታሪካዊት ገዳም በእነብሴ ሳር ምድር ወረዳ ርዕሰ ከተማ የምትገኝ ሲሆን ከወረዳው ጋር የሚዋሰኑ በምሥራቅ ደቡብ ወሎ ዞን፣ በምዕራብ ጎንቻ ሲሶ እነሴ ወረዳ ፣ በሰሜን ደቡብ ጎንደር ዞን፣ በደቡብ እናርጅ እናውጋ ወረዳ የሚያዋስኗት ታላቅ ገዳም ስትሆን መርጡለ ማርያም ለእነብሴ ሳር ምድር ወረዳ ርዕሰ ከተማ መጠሪያ ስምም ሆና በማገልግል ላይ ትገኛለች ::

በገዳሟ ህግና ሥርዓት መሠረት ርዕስ ርዑሳን ተብለው እየተሾሙ ገዳሟን ያገለገሉ አስተዳዳሪዎች ስም ዝርዝር ቅደም ተከተል በከፊል

የኦሪቱን ሊቀ ካህናት ሚናስን በኤጲስ ቆጶስነት ማዕርግ ርዕሰ ርዑሳን በአቡነ ሰላማ ከሳቴ ብርሃን የመጀመሪያው ርዕሰ ርዑሳን ናቸው
መምህር ኪዳነ ማርያም
መምህር ቢኖር
መምህር ወልደ ሴም
መመህር ወልደ ሚካኤል
መምህር ወልደ ማርያም
መምህር እሸቴ
መምህር እንግዳ
መምህር ክንፈ ሚካኤል
መምህር ሳህሉ
መምህር ዘውዱ
መምህር ወልደ ኤወስጣቴወስ
መምህር ሐብተ ድንግል
መምህር ገብረ ሚካኤል
መመህር ጸኃይ
መመህር ክንፉ
መምህር ካሳ አየለ / ቅዱሱ/
መምህር ውቤ
መምህር ወልደ ጊወርጊስ
መምህር አሰገነኝ
መምህር ፊላታኦስ። ከተራ ቁጥር 2 እስከ ተራ ቁጥር 21 ድረስ ያሉ የገዳሟ አስተዳዳሪ በመሆን መምህር እየተባሉ ሲጠሩ የቆዩ ሲሆን ምክንያቱም ራስ ኃይሉ ተክለ ሃይማኖት ርዕሰ ርዑሳን የሚለው መጠሪያ ስም የኔነው ብለው ስላሉ ስሙን ወስደውታል። በመሆኑም ከዚህ ቀጥለው የተሸሙት ርዕሰ ርዑሳን አባ ላዕከ ማርያም አየለ ተከራክረው ስያሜውን አስመልሰውታል። እርሳቸውን ጨምሮ ከሳቸውም ቀጥሉ እንደሚከተለው ነው፡
ዕሰ ርዑሳን አባ ላዕከ ማርያም አየለ
ርዕሰ ርዑሳን አባ ኃይለ ኢየሱስ ገብረማርያም
ርዕሰ ርዑሳን አባ ወልደ ማርያም አማረ
ርዕሰ ርዑሳን አባ ሀብተ ሚካኤል ታደሰ
ርዕሰ ርዑሳን አባ ሃይለ ማርያም ታገለ
ርዕሰ ርዑሳን አባ ተክለ ማርያም ባዩ
ርዕሰ ርዑሳን አባ ወልደ መድኅን ታዴ
ርዕሰ ርዑሳን አባ ገብረ ማርያም ገረመው
https://am.sewasew.com/p/%E1%89%B3%E1%88%AA%E1%8A%AB%E1%8B%8A%E1%89%B7%E1%8A%95-%E1%88%98%E1%88%AD%E1%8C%A1%E1%88%88-%E1%88%9B%E1%88%AD%E1%8B%AB%E1%88%9D-%E1%8C%88%E1%8B%B3%E1%88%9D-%E1%88%AD%E1%8B%95%E1%88%B0-%E1%88%AD%E1%8B%91%E1%88%B3%E1%8A%95-%E1%89%B0%E1%89%A5%E1%88%88%E1%8B%8D-%E1%8A%A5%E1%8B%A8%E1%89%B0%E1%88%BE%E1%88%99-%E1%8B%AB%E1%8C%88%E1%88%88%E1%8C%88%E1%88%89-%E1%8A%A0%E1%88%B5%E1%89%B0%E1%8B%B3%E1%8B%B3%E1%88%AA%E1%8B%8E%E1%89%BD-%E1%8B%9D%E1%88%AD%E1%8B%9D%E1%88%AD

08/13/2023

የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ህገ-መንግሥት
====
በዚህ ሳምንት ውስጥ ሆነው ካለፉ የታሪክ ክስተቶች መካከል በዛሬው ሳምንቱን በታሪክ ዓምዳችን የምንቃኘው የኢትዮጵያን የመጀመሪያ ህገ መንግሥት ይሆናል። በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ የተፃፈ የመጀመሪያ ህገመንግሥት ይፋ የተደረገው ሐምሌ 9 ቀን 1923 ነበር። ህገ መንግሥቱ እንዴት ተዘጋጀ፣ ምን ምን ጉዳዮች ይዞ ነበር የሚሉና ሌሎች መሰል ጉዳዮችን እንዳስሳለን።

ኢትዮጵያ በዘመናዊ መንግሥት ሥርዓት መተዳደር ከጀመረች ጊዜ አንስቶ የተለያዩ ህጎች፣ደንቦችና መመሪያዎች እየወጡ ሲሰራባቸው ቢቆይም፣ በንጉሰ ነገስት ቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ ከፀደቀው ከዚህ ህገ መንግሥት በፊት ተፅፎ የተቀመጠና የአገሪቱ ስርዓተ መንግሥት የሚመራበት ሰነድ አልነበረም።

በእርግጥ ከዚህ ህገ መንግሥት በፊት ፍትሀ ነገስት የሚባልና በነገስታት የሚሰጡ መተዳደሪያ ትእዛዞች ህጎች መመሪያዎች ያቀፈ ያልተጠረዘ ሰነድ እንደነበር የተለያዩ ሰነዶች ያስረዳሉ። ይህ ህገ መንግሥት ረቆ ተግባር ላይ እንዲውል ያደረጉት ቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ በወቅቱ ህገ መንግሥቱን ማርቀቅና ሥራ ላይ ማዋል ስላስፈለገበት ምክንያት አስረድተውም ነበር። በዚህም የህገ መንግሥቱ ሥራ ላይ መዋል አስፈላጊነት ሲገልፁ አገሪቱ በህገ መንግሥት እንድትመራና ሌሎች ከንጉሱ በታች ያሉ ባለስልጣናት ለዚህ ህገ መንግሥት እንዲገዙና ህዝብ የመንግሥትን ሥራ እንዲያውቀውና በዚያ ውስጥ ተሳታፊ እንዲሆን ለማስቻል እንደነበር ገልፀዋል።

ንጉሱ ለአገሪቱ ህገ መንግሥት ያስፈልጋታል ብለው አምነው ወደ ተግባር ሲንቀሳቀሱ ህገ መንግሥቱን እንዲያዘጋጁ አልያም ደግም እንዲያረቁ ሁለት ሁነኛ ሰዎችን መርጠው ነበር። በማርቀቅ ሂደት ተመርጠው የተሳተፉት ተክለ ሀዋሪያት ተክለ ማሪያምና ብላቴ ጌታ ህሩይ ወልደ ስላሴ ነበሩ።

በህገ መንግሥቱ የማርቀቅ ሂደት ውስጥ ብዙ ክርክርና አለመግባባቶችም ተነስተው እንደነበር የታሪክ መዛግብት ይገልፃሉ። ህግ መንግሥቱ በወቅቱ ከነበረው የጃፓን ህገ መንግሥት ብዙ ጉዳዮችን ተወስዶ የተዘጋጀ ሲሆን፣ በኢትዮጵያዊ ህዝብና ባህል መሰረት ባደረገ መልኩ እንዲጣጣም የተለያዩ ጉዳዮች ላይ ማስተካከያ ተደርጎበታል። በእርግጥ በወቅቱ በወጣው ህገ መንግሥት ላይ የንጉሱ ሹማምንትና ባለስልጣናት በህገ መንግሥቱ ላይ ብዙ ጥያቄዎችን አንስተው አለመግባባት ውስጥ ገብተው ነበር።

በተለይም በስልጣንና በመሬት ባለቤትነት ዙሪያ የተለያዩ ሀሳቦች ተነስተው ነበር። ከወቅቱ መሳፍንት አብዛኛዎቹ ኢትዮጵያ ውስጥ ስልጣንና መሬት ለመሳፍንት፣ለመሳፍንት ልጆችና ልጅ ልጆች ብቻ መከፋፈል አለበት ብለው ያምኑ ነበር። በአንፃሩ ደግሞ መኳንንቶች የመሳፍንቱን ሀሳብ በመቃወም በኢትዮጵያ መሬትና ግዛት ውስጥ እስከኖረ ድረስ ሌላውም ሰው መብት ሊኖረው ይገባል የሚል ሀሳብ አንስተዋል።
በመጨረሻም በዚህ ሙግትና የተለያዩ ሀሳቦች መሀል የተዘጋጀውና የረቀቀው ህገ መንግሥት ለቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ ቀርቦ ንጉሱ የመሳፍንቱን ሀሳብ ውድቅ አድርገው የመንግሥት አገልጋዮችና ህዝቡ የመብቱ ተጠቃሚ መሆን እንዳለባቸው በህገ መንግሥቱ ውስጥ እንዲካተት አድርገዋል።

ይህ ህገ መንግሥት ምንም እንኳን የመንግሥትና የሀይማኖት መለያየትን አለመግለፁ፣ የንጉሱ ስልጣን ገደብ በመለጠጡና፣ በተጠያቂነት ረገድ ዴሞክራሲያዊ አለመሆኑ በብዙዎች ቢተችም እንደ አገር ተረቆና በህግ ደረጃ ሊተገበር ታስቦ ሥራ ላይ በመዋሉ ብቻ አድናቆትን ይቸሩታል። ይህ ብዙ ችግሮች ነበሩበት የተሰኘው ህገ መንግሥት በሥሩ 11 ምዕራፎችና 85 አንቀፆችን ይዟል።

ይህ የመጀመሪያ የኢትዮጵያ ዘመናዊ ህገ-መንግሥት ቀደም ብሎ የነበረውን ፍትሀ ነገስትን ለመተካት የመጣ ህገ-መንግሥት ነበር። በሐምሌ 9 ቀን 1923 ዓ.ም የተካሄደ ታላቅ ድግስ ላይ ነው እንዲጸድቅ የተደረገውም። በህገ መንግሥቱም ስለ ስልጣን ርክክብ ሁኔታዎች፣ ስለ አልጋ ወራሾች፣ የኃይለስላሴ(ንጉሱ) ስልጣን፣ስለግዴታዎች እና በኃይለስላሴ እውቅና ስለተሰጣቸው መብቶች፣ ስለ ኢትዮጵያ ፓርላማ፣ ስለ ሚኒስቴሮች እና የሥራ በጀት አወጣጥ የመሳሰሉ ዋና ዋና ሀሳቦች የተካተቱበት ነበር።

በህገ መንግሥቱ ላይ የተመለከቱ ዋና ዋና ነጥቦች ለመጥቀስ ያህል የኢትዮጵያ ወሰን ከጫፍ እስከ ጫፍ ድረስ ያለው የንጉሰ ነገስቱ እንደሆነ፣ ማንኛውም የኢትዮጵያ ህዝብ በአንድነት የኢትዮጵያ ህዝብ እንደሚባል፣ የኢትዮጵያ ህዝቡም መሬቱም ሁሉ የንጉሰ ነገስቱ እንደሆነ፣የኢትዮጵያ ንጉሰ ነገስት መሆን የሚችለው ከንጉስ ሰለሞንና ከንግስተ ሳባ የመጣው የቀዳማዊ ሚኒልክ የዘር ሀረግ ከአፄ ሀይለ ስላሴ ዘር የተገኘ መሆን አለበት የሚለውና የንጉሰ ነገስቱ ክብር የማይቀነስ፣ ማዕረጉ የማይገሰስ መሆኑን በጥብቅ የሚገልፁ አናቅፆች ነበሩት።

በህገ መንግሥቱ ላይ ጥያቄ የሚያስነሱ እና በዚህ ዘመን እይታ የሚተቹ ብዙ አንቀፆችና ህጎች የተካተቱበት ነበር ከሚያሰኙ ጉዳዮች ዋንኛው ንጉሰ ነገስቱ ስልጣናቸው (ንግስናቸው) በፍፁም በሌላ አካል እንዳይነጠቁ የሚያዘውና ስልጣናቸውን ቀጣይነት እንዲኖረው የሚያደርጉ መሆናቸው ነው። ይህ ህገ መንግሥት እስከ 1955 ድረስ ቆይቶ በሌላ ተለውጧል።

ተገኝ ብሩ

አዲስ ዘመን ሐምሌ 11/2013
https://am.sewasew.com/p/የመጀመሪያው-የኢትዮጵያ-ህገ-መንግሥት

08/12/2023

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን የፓትርያርክ ስልጣኗን ለማግኘት ከግብፅ ቤተክርስትያን ጋር ያረገቸው ተጋድሎ ምን ይመስል ነበር?የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ፓትርያርክስ ማን ናቸው?
=====
በፍትሐ ነግስቱ ዓንቀጽ 4፣ ቁጥር 50 መሰረት የግብፅ አለክሳንድርያ ቤተ ከርስትያን ለ1600 አመታት ያህል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያንን ሹማ በመትልከው ሊቀ ጳጳስ አማካኝነት ስታስተዳድር ቆይታለች። ይህም ዓንቀጽ እንዲህ ይላል:
'የኢትጵያ ሰዎች ከዐዋቂዎቻቸው ወገን በራሳቸው ፈቃድ ሊቀ ጳጳሳትን ለራሳቸው አይሹሙ። ጳጳሳቸው ከስክንድርያው በዓለ መንደር ስልጣን በታች ነውና። ከሊቀ ጳጳሳት በታች የሆነውን ሊቀ ጳጳስ ከእርሱ ወገን ሊሾምላቸው የሚገባውም እርሱ ነው'
ኢትዮጵያዊያን አባቶች ይህ አሰራር ቀርቶ ቤተክርስትያኗ ከራሷ አብራክ በተከፈሉ እና በምእመናኗ ቇንቇ በሚናገሩ ኢትዮጵያውያን አባቶች ትመራ ዘንድ ከፍተኛ ትግል ሲያደርጉ ቆይተዋል። የታሪክ መዛግብት እንደሚያመለክቱት 'ቁጥራቸው ብዙ ለሆነው የኢትዮጵያ ቤተክርስትያን ምእመናን በራሳቸው ቇንቇ ተዟዙሮ የሚያስተምራቸው ኢትዮጵያውያን እፒስ ቆጶሳት ያስፈልጋቸዋል' ብሎ ለመጀመሪያ ጊዜ ድምፁን ያሰማው የኢትዮጵያ ንጉስ ቅዱስ ሐርቤ (1060 እስከ 1077) ነበር። በጊዜውም ለነበረው ግብፃዊ የኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ (አባ ሚካኤል) ጥያቄውን ቢያቀርብም፣ ሊቀጳጳሱ ግብፅ ካሉት ፓትርያርክ ጋር መክሮ ጥያቄውን ውድቅ አድርገውበታል። ከንጉስ ሐርቤም ቀጥሎ ያሉት ነገስታት ምንም እንኯን አዎንታዊ መልስ ባያገኙም ጥያቄያቸውን በግብፅ ለነገሱ የእስላም ነገስታት አቅርበዋል።

ወደ 19ኛው መካከለኛ ክፍለ ዘመን ስንመጣም አፄ ሚንልክ ከነገሱ በሇላ ይሄው የኢትዮጵያውያኑ ጥያቄ በአማርኛ ቇንቇ እየተዘጋጁ ይታተሙ የነበሩትን 'አእምሮ' ና 'ብርሃንና ሰላም' የተሰኙ ጋዜጦችን ሽፋን እያገኘ፣ ሊቃውንቱም በህትመቶች ሀሳባቸውን እየገለፁ ሄዱ። በዚህም ምክንያት ነገሩ እየጠነከረ መጣ።

በልዑል አልጋ ወራሽነት መዓረግ ባለ ሙሉ ስልጣን እንደራሴ የነበሩት ራስ ተፈሪ መኮንን (በሇላ ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ) ከጊዜ ወደ ጊዜ የነገሩን ጥንካሬ ማግኘት በመገንዘብ አጀንዳው የቤተመንግስቱ እንዲሆን አደረጉ። ከዚህም በሇላ ከግብፅ ቤተክርስትያን ፓትርያርክ ጋር ባደረጉት ብዙ የቴለግራም ልውውጥ በሇላ 'ብዙ ኢትዮጵያውያን ጳጳሳት ይሾሙልን' ብለው ያቀርቡት ጥያቄ የሚከተለውን የቴለግራም መልስ አግኝቷል:
'ከኢትዮጵያ መምህራን አምስት ሰዎች ተመርጠው ጳጳሳት ሆነው አምስት የኢትዮጵያ እጲስ ቆጶሳት ሹመት እንዲሾሙ ፈቅደናል፤ አምስት መነኮሳት እንዲልኩልን እንለምናለን '
በዚህም ፈቃድ መሰረት አምስት አባቶች ማለትም ብፁዕ እጨጌ ገብረ መንፈስ ቅዱስ፣ መምህር ደስታ፣ መምህር ኃይለ ማርያም፣ መምህር ወልደ ኪዳንና መምህር ኃይለ ሚካኤል ተመርጠው፣ ነገር ግን ብፁእ እጨጌ ገብረ መንፈስ ቅዱስ በህመም ምክንያት ቀርተው፤ አራቱ አባት አቡነ ጴጥሮስ፣ አቡነ አብረሃም፣ አቡነ ይስሐቅና አቡነ ሚካኤል ተብለው በ 1921 ዓም ግብፅ ላይ ተሾሙ። እንግዲህ አርበኛው እየተባሉ የሚጠሩትና በኢጣልያን መንግስት የተገደሉት አቡነ ጴጥሮስ አንዱ ነበሩ ማለት ነው።

እንዲህ እያለ በውቅቱ የኢጣልያ ወረራ ይመጣና በወቅቱ የኢትጶጵያ ሊቀ ጳጳሳት የነበሩት ግብፃዊው አቡነ ቄርሎስ በጦርነቱ ምክንያት ሹመቱን በተጠባባቂ ሊቀ ጳጳስነት ለኢትዮጵያዊው አባት ለአቡነ አብረሃም ሰተው ወደ ግብፅ ይገባሉ። ይህ በእንዲህ እያለ የኢጣልያ መንግስት በቤተክርስትያናችን ላይ የፈፀውን ግፍ ለማስረሳት በዚህም እሷን መሳሪያ አድርጎ በየቦታው የእግር እሳት የሆኑበትን አርበኞችን ለማስታገስ ሲል በ1930 ዓም የኢትዮጵያ ቤተክርስትያን የራሷን ሊቀ ጳጳሳትና እጲሥ ቆጶሳት መሾም ትችላለች በማለት ዐወጀ። በዚህም ምክንያት ከተለያዩ ክፍለ ሃገራት የተውጣጡ አባቶች የተሳተፉበት ጉባኤ ተደርጎ ውይይት ተደርጎ ቀደም ሲል ወደ ግብፅ ሂደው የተሾሙትን አቡነ አብርሃምን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስትያን ሊቀ ጳጳሳት እንዲሆኑ እና ሊሎች ጳጳሳት እና ኤጲስ ቆጶሳት እንዲሾሙ የሚል ታሪካዊ ውሳኔ አሳልፏል።

ኢትዮጵያውያን ችግር ባጋጠማቸው ጊዜ በአቡነ ቄርሎስ አማካኝነት ሀገሪቷን የሸሸችው የግብፅ ቤተክርስትያንም ይህንን ሹመት በሰማች ጊዜ ድርጊቱንም ሆነ የድርጊቱን አስፈጻሚ አቡነ አብርሃምን አወገዘች። ከውግዘትም ጋር ህዝቡ ከእሳቸውም ሆነ እሳቸው ከሾሟቸው አባቶች መስቀል እንዳይሳለም ጥሪ አቀረበች። ነገር ግን ኢትዮያውያኑ አባቶች እንዲሁም ምእመኑ ለውግዘቱ ቦታ ሣይሠጡ አገልግሎታቸውን ቀጠሉ። ከዓመት በሇላ ሐምሌ 14 ቀን 1931 ዓም ሽምግልና ተጭጫኗቸው የነበሩት ብፁዕ አቡነ አብርሃም ዐረፉ። በመሁኑም በእርሳቸው ቦታ የሚተካውን ሊቀ ጳጳስ ለመምረጥ ከየክፍሉ የተውጣጡ ሊቃውንት ቤተ ክርስትያን መስከረም 1 ቀን 1932 ዓ ም እንደ ገና ጉባ ዔ አድርገው አቡነ ዮሐንሥን መንበረ ሊቀ ጵጵስናውን እንዲረከቡ ፣ እርሳቸውም ሊሎ ች ጳጳሳትን እንዲሾሙ ተመረጡ ።

እግዚአብሔር በአምስቱ የመከራ ዘመናት በየቦታው የፈሰሰውን የንጹሐን ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት ደም ጩኸት፤ እንዲሁም በየዋሻው ዘግተው የሚጸልዩትን አባቶችና እናቶ ች ጸሎት ሰምቶ በ1933 ዓም ሀገሪቷ ከወራሪው ኃይል ነጻ ወጣች። ንጉሡም ወደ ኢትዮጵያ ተመለሱ። በዚህ ጊዜ የሁለቱን ወዳጅ ሀገሮች (የግብፅንንና የኢትዮጵያን) ፓለቲካዊ ግንኙነት ለመጠ በቅ በሚል በወቅቱ የተሾሙት አባቶች በየሀገረ ስብከታቸው ያለ ምንም ሥራ እንዲቀመጡ ሆ። የቤተ ክህነቱንም ሥራ በወቅቱ የደብረ ሊባኖስ ገዳም ዕጨጌ የነበሩት ዕጨጌ ገብረ ጊዮርጊስ እንዲመሩት ተደረገ።

ከዚህ በኋላ ግርማዊ ንጉሠ ነገሥቱ ተቋርጦ የቆየው የሁለቱ አብያተ ክርስትያኑ ግንኙነት እንዲቀጥል ለግብፅ ቤተ ክርስቲያን ጥያቄ አቀረበች። በጥያቄውም መሠረት የግብፅ ቤተ ክርስቲያን በወረራው ወቅት ሸሽተው ወደ ሀገራቸው በሔዱት አቡነ ቄርሎስ የሚመራ አንድ ልኡከ ወደ ኢትዮጵያ ላከች። ልዑኩ በቤተ መንግሥቱ ከተወከሉ ኢትዮጵያውያን ጋር ከተወያየ በኋላ የኢትዮጵያን "ግዝቱ ይነሣልን" ጥያቄ ይዞ ወደ ካይሮ ተመለሰ። በዚህ ጊዜ አቡነ ቄርሎስ አዲስ አበባ ቀሩ። ጉዳዩን መስመር ለማስያዝ በሚልም በወቅቱ የሊቀ ጳጳሳትነቱን ቦታ ይዘው የነበሩት ብፁዕ አቡነ ዮሐንስ የመንበረ ሊቀ ጳጳሱን ግቢ እንዲለቁ ተደርጎ ግብፃዊው ሊቀ ጳጳሳት በዚያ እንዲቀመጡ ተደረገ።

አቡነ ቄርሎስ አዲስ አበባ ተቀምጠው በሁለቱ ቤተክርስትያናት እንዲሁም በቤተ መንግስቱ መካከል ልዑካን ቢመላለሱም ነገሩ የኢትዮጵያ ኦሮቶዶክስ ቤተ ክርስትያን በምትፈልገው መልኩ ሊሄድ አልቻለም። ቀድሞ በመከራ ዘመን የግብፅ ቤተ ክርስቲያን ባደረገችው ፊትን የማዞር ድርጊት፤ ከነጻነትም በኋላ ግዞቱን ላለማንሳት እየሰጠችው ባለው ሐላፊነት የጎደለው መልሰ ክፉኛ ያዘነው የመንፈሳዊ ጉባኤውም በመደበኛ አማካሪዎቹ አማካይነት አዲስ አበባ ላይ ሰፊ ውይይት ያዘ፡፡ በጉዳዩ ላይ በስፋት ከ ተወያየበት በኋላም ሐምሌ 6 ቀን 1937 ዓም አንድ ከባድ ውሳኔ አሳለፊ። ይኸውም "የግብፅ ቤተ ክርስቲያን እየተደረገ ባለው ውይይት ያሳለፈችውን ግዝት ታንሣ። ከአሁን በኋላም የግብፅን ቤተ ክርስቲያን እምነት ባንለውጥም ከግብፅ ምንም ዓይነት ሊቀ ጳጰሳትን አንፈልግም። በቋንቋችን የሚናገርና የሚያስተምር ሊቀ ጳጳሳት እ ንፈልጋለን" የሚል ነበር። የውሳኔው ሙሉ ቃል በእጨጌ ገብረ ጊዮርጊስ እንዲፈረምበት ከተደረገ በኋላ ለንጉሠ ነገሥቱ ተላከ።

ከወራት በኋላም ኅዳር 9 ቀን 1938 ዓም ጠቅላላ መን ፊሳዊ ጉባኤው እንደገና ተሰበሰበ። በዚህም መሠረት ባለፉት ጊዜያት የተደረጉትን ውይይቶችና የተከናወኑትን ድርጊቶች ሪፖርት በመስማት በሐምሌ የአማካሪዎች ጉባኤ ያስተላለፈውን ውሳኔ በመቀ በል ተጨማሪ የውሳኔ አሳቦችንና ማሳሰቢያዎች በማስተላለፍ ተበተነ።

በዚህ የሊቃውንቱ ቆራጥ ዐቋም የተነሣም በችግር ጊዜ ወደሃገራ ቸው ሸሽተው ሔደው የነበሩትና በኢትዮጵያውያን አባቶች ሊቃውንት እንዲሁም አርበኞች ደም ሰላም ከመጣ በኋላ ተመልሰው መጥተው የነበሩት አቡነ ቄርሎስ ኢትዮጵያን ለቀው ሄዱ። ከላይ በተገለጠው ዓይነት የተላለፈው የመንፈሳዊ ጉባኤው የመጨረሻ ውሳኔ የደረሰው ቤተ መንግሥትም በጉዳዩ ላይ ከመከራ በኋላ ከመንፈሳዊ ጉባኤው አቋም ለየት ያለ አሳብ አቀረበ፡፡ ይህውም ከግብፅ ቤተ ክርስቲያን ጋር በዚህ ዓይነት ከምንለያይ ለተጨማሪ ውይይት ጊዜ መስጠት ይኖርብናል የሚል ነበር። ቤተ መንግሥቱ ይህንን አሳቡንም በፅጨጌ ገብረ ጊዮርጊስና፡ በሌሎች አማካይነት ለመንፈሳዊ ጉባኤው ገለጸ።

የሊቃውንቱ ጉባኤ ምንም እንኯን "አስከመቸ እ ንወያያለን?" በሚል በተወሰነ ደረጃ የቤተ መንግሥቱን ጥያቄ ላለመቀበል ተቃውሞ ቢያሰማም በመጨረሻ ግን "ይሁን፣ ጥቂት ጊዜ ይሰጥ" በሚል ተስማማ። አቋሙ አንዳልተቀየረ፣ ጥያቄው ተግባራዊ ይሆን ዘንድ ብቻም ተጨማሪ ጊዜ እንደ ሰጠ በመግለጽ አንደ ገና በእጨጌ ገብረ ጊዮርጊስ ፊርማ ለቤተ መንግሥቱ አቀረበ። በዚህ ደብዳቤ የሚከተለው ሃሳብ ተካቶበታል።

"... መላው ጉባኤ በኢትዮጵያ የሚገቡት ነገሮች እንዲሰጡ ሊቀ ጳጳሳትም ከኢትየጵያ ተወላጆች ውስጥ እንዲመረጥ ማስፈለጉን ተስማምቶበታል። ይኸውም እሳብ በመንግሥታችን ወገን የተደገፈ ስለሆነ መንግሥታቸን መልእክተኞችን ልኮ እሳቡን ለማስፈጸም የሚከናወንለት ክሆነ ጉባኤው ተቃዋሚ እይደለም፤ ስለዚህ የቤተ መንግሥታቸን እሳብና ምኞት መልእክተኞቹን ልኮ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የጠየቀችውን ሁሉ በእስክንድርያው ፓትርያርክ ተጠባባቂ ወይም ከጉባኤው
ጋር በሰላም ለመጨረስ ስለሆነ ይህንኑ በቶሎ በፍጻሜ እንዲያደርስላት የኢትዮጵያ ቤተ ክርስተያን ግርማዊነትዎን በጸሎት እየደገፈች ትለምናለች። ነገር ግን ግርማዊነትዎ መልእክተኞችን ልኮ ከአሁን በፊት በዚሁ ነገር ቤተ ክህነት የደከመችውን ያህል በነገሩ ደክመውበት በእስክንድርያው ፓትርያርክ ተጠባባቂ ወይም በጉባኤው ፍሬ ያለው ምላሽ ያልተገኘ እንደሆነ ግርማ ዊነትዎ የተስማማ እንደሆነ ባለመጠራጠር እናምናለን፡፡"

ቤተ መንግሥቱም ይህንን የመሰለ ጠንካራ ማሳሰቢያ ከቤተ ክርስቲያኗ ሊቃውንት ከተቀበለ በኋላ በጉዳዩ ላይ ከግብፅ ቤተ ክርስቲያን ጋር መክረው የኢትዮጵያን ጥያቄ ያሰፈጽሙ ዘንድ ክቡር ፊታውራሪ ታፈሰ ሀብተ ሚካኤልንና ብላታ መርሥዒ ኀዘን ወልደ ቂርቆስን ጥር 1 ቀን 1938 ዓም ወደ ካይሮ ላከች። ልዑኩ ወደዚያ ሲሔድ ከንጉሠ ነገሥቱ ዘንድ ለፓትርያርኩ የተጻፈ ደብዳቤ ይዞ ነበር። ጉዳዩ በኢትዮጵያውያን ሊቃውንት ዘንድ ተጠናክሮ መቀጠሉ ን የሰማው የግብፅ ቤተ ክርስቲያን ሲኖዶስ ግን ኢትዮጵያውያኑ ልዑካን ካይሮ ከመድሪሳቸዐኑ በፊት አንድ ውሳኔ አሳለፈ። ያህውም ለሚሾሙት ኢትዮጵያውያን ጳጳሳት ጋር ሁለት የግብፅ ጳጳሳትም ተሹመው ወደ ኢትዮጵያ ይምጡ የሚል ነበር።

ከባድና ታሪካዊ ተልዕኮ ይዘው የሄዱት ሁለቱ ልዑካንም ካይሮ እንደደረሱ ውሳኔው ተገለጸላቸው። ይሁን እንጂ በቀረበ ላቸው ውሳኔ ባለመስማማት ክርክራቸውን ቀጠሉ። ከብዙ ክርክርና ውይይት በኋላም የግብፅ ቤተ ክርስትያን የኢትዮጵያን ጥያቄ እንደ ተቀበለች፣ በጥያቂው መሠረትም የኢትዮጵያውያኑ አባቶች ሹመት በግንቦት ወር ለሚደረገው የአዲስ ፓትርያርክ ሹመት ጋር እንደሚፈፀም ለዚያም አምስት አባቶች ተመርጠው እንዲላኩ ለልዑካኑ ተገለጸላቸው።

በውሳኔውም መሠረት የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት በዕውቀት እና በምግባር የተመሰከረላቸው አምስት ሊቃውንት መርጠው በፊታውራሪ ታፈሰ ሀብተ ሚካኤልና በብላታ መርሥዔ ኀዘን ወልደ ቂርቆስ መሪነት ሚያዝያ 28 ቀን 1938 ዓም ወደ ካይሮ ላኩ። የግብፅ ቢተ ክርስትያን አስቀድማ በገባችው ቃል ኪዳን መሰረት የግብፅ 115ኛ ፓትርያርክ ከሆኑት አቡነ ዮሳብ ጋር ግንቦት 2 ቀን 1938 ዓም ሊሾሙ ወደ ካይሮ የገሰገሱት አባቶች በሰላም ገብተው ዝግጁነታቸውን ገለጡ። ነገር ግን ባልጠበቁት ሁኔታ በግብፆች የተዘጋጀና የኢትዮጵያ ቤተክርስትያን ሙሉ በሙሉ ነፃነቷን እንዳታውጅ የሚያደርግ ሰነድ ቀረበላቸው። ሰነዱም የሚሾሙት ጳጳሳት ወደ ኢትዮጵያ ሲመለሱ ሌላ ኤጲስ ቆጶስ እንዳይሾሙ የሚያግድ ሲሆን ኢትዮጵያውያኑ አባቶች ከመሾማቸው በፊት እንዲፈርሙበት ይጠይቃል። የግብፆችን ተንኮል በሚገባ የተረዱት አባቶችም ሲኖዶሱ ያሳላፈውን ውሳኔ ባለመቀበል ተቃውሞዋቸውን በፊታውራሪ ታፈሰ ፊርማ ለተጠባባቂ ፓትርያርኩ አሳወቁ። ወዲያውኑ ሲኖዶሱ ያቆያቸውን ውሳኔ በተጠባባቂ ፓትርያርኩ በኩል ለግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ እንዲላክ አደረጉ። ንጉሰ ነገሥቱም ውሳኔውን በሚገባ ከመረመሩ በኋላ ኢትዮጵያ የማስማማባቸውን ነጥቦች በዝርዝር በማስቀመጥ ኢትዮጵያኑ ልዑካን ካፓትርያርኩ ጋር ይወያዩባቸው ዘንድ ለፊታውራሪ ታፈሰ ላኩላቸው። ይህንንም እንዳደርጉ ለፓትርያርኩ በደብዳቤ አሳወቁ። የንጉሱ ደብዳቤ የደረሳቸው ተጠባባቂ ፓትርያርክም ለንጉሱ የመልስ ደብዳቤ ከፃፉ በኋላ ከልዑካኑ ጋራ የጋራ ስብሰባ አድረገው ተዋያዩ። ከውይይቱም በኋላ ኢትዮጵያውያኑ አባቶች አዲሱ ፓትርያርክ ከመሾማቸው በፊት ሊሾሙ አይቻልም ከሚል ውሳኔ ላይ ስለደረሱ እና አንዳንድ ተጨማሪ ግልፅ ያልሆኖ አሳቦች ስለ ነበሩ ተጠባባቂ ፓትርያርኩን በመሰናበት ከወራት ፍሬ ቢስ ቆይታ በኋላ ሐምሌ 29 1938 ዓም ወደ ኢትዮጵያ ተመለሱ። በዚህ የተነሳ ከግብፅ ቤተ ክርስትያን ጋር የነበረው ግንኙነት ለሁለት አመታት ያህል ተቋረጠ። ይህንን በያሉበት ሆነው የሰሙት ኢትዮጵያውያኑ ሊቃቅንትና መምህራን ምንም እንኳን እንዳለፉት አይነት ጉባኤያት አድረገው ባይወያዩም በያሉበት ሆነው ድምፃቸውን ሲያሰሙ ቆዩ።

የሊቃውንቱ ድምፅ ከፍ እያለ እንደ ገና ጉባኤ ወደ መጥራት አዝማሚያ ሲደርስ ሀምሌ 9 1940 ዓም የግብፅ ቤተ ክርስትያን ፓትርያርክ አቡነ ዮሳብ ለግርማዊ ንጉሰ ነገሥቱ አንድ መልእክት ላኩ። መልእክቱም የግብፅ ቤተ ክርስትያን ኢትዮጵያውያኑን አባቶች ለመሾም መወሰኗን የሚገልጥ ነበር። በዚህም መሰረት ከሁለት አመታት በፊት ተመርጠው ይሾሙ ዘንድ ወደ ካይሮ ሄደው የነበሩት አምስት አባቶች እንደ ገና ወደ ካይሮ ሄዱ። እንደ ደረሱም ኢትዮጵያውያኑ በተስማሙበት አንድ ፕሮቶኮል ላይ ፈርመው ሐምሌ 18 ቀን 1940 ዓም ካይሮ ላይ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ዮሳብ እጅ ተቀብተው ጳጳሳት ሆኑ። ከተፈራረሙትም ፕሮቶኮል ውስጥ "አንድ ኢትዮጵያዊ ሊቀ ጳጳሳት ከመሾሙ በፊት አሁን በኦፊሴል ሊቀ ጳጳሳት ዘኢትይዮጵያ ተብለው የሚታወቁት ብፁዕ አቡነ ቄርሎስ ማረፍ አለባቸው" የሚል ይገኝበታል።

ሐምሌ 18 ቀን 1940 ዓም ስርአተ ሲመት ተፈፅሞላቸው ሐምሌ 22 ቀን 1940 ዓም አዲስ አበባ የገቡት ኢትዮጵያውያን አባቶች የሚከተሉት ነበሩ።
ብፁዕ እጨጌ ገብረ ጊዮርጊስ - አቡነ ባስልዮስ
መምህር ገሪማ ወልደ ኪዳን - አቡነ ሚካኤል
ሊቀ ስልጣናት መልእክቱ ወልደ ማርያም - አቡነ ባስልዮስ
መምህር ዘፈረ ብርሃን ገብረ ፃዲቅ - አቡነ ያዕቆብ
መምህር ጌታሁን ወልደ ሐዋርያት - አቡነ ጢሞቲዎስ

ከሦስት አመታት በኋላ ግብፃዊው የኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳሳት አቡነ ቄርሎስ ሲያርፉ ቀደም ሲል በተፈረመው ፕሮቶኮል መሰረት ብፁዕ አቡነ ባስልዮስ በብፁዕ አቡነ ዮሳብ የኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳሳት ሆነው ተሾሙ። ይህም ለዘመናት እልህ አስጨራሽ ክርክር ላደረገቸው የኢትዮጵያ ቤተ ክርስትያን ቤተ መንግስት ከፍ ያለ ደስታን ፈጠረ።

የኢትዮጵያ ቤተ ክርስትያንም ከዚያ በኋላ እንደ ፍላጎቷና እንደ ሕዝቧ ጥያቄ ኤጲስ ቆጶሳትንና ጳጳሳትን እየሾመች ለአገልግሎት በማሰማራት የስብከተ ወንጌል አገልግሎቷን ማስፋፋቷን ቀጠለች። ይህ በእንዲህ እንዳለ በ1948 ዓም በግብፅ ቤተ ክርስትያንቅዱስ ሲኖዶስ አባላት መካከል መለያየት ተከሰተ። በዚህም የተነሳ ፓትርያርኩን በተቃወሙ አባላት ምክንያት የግብፅ ቤተ ክርስትያን ፓትርያርክ የነበሩትና የሁለቱን እህት አብያተ ክርስትያናት ወደ ላቀ ደረጃ ያደረሱት ብፁዕ አቡነ ዮሳብ ከመንበረ ፓትርያርክነታቸው ተነሱ። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስትያን ይህንን ድርጊት በመቃወም ድምጿን አሰማች። አንድ በጉዳዩ መክሮ የሚመለስ ልዑክም ወደ ካይሮ ላከች። ይሁን እንጂ ፓትርያርኩን ከመንበራቸው ባወረዷቸው አባቶች እምቢታ የተነሳ ልኡኩ ያላ ውጤት ተመለሰ።

የኢትዮጵያ ቤተ ክርስትያን ይህ እና ሌላም አንድ ልዑኳ ካለ ፍሬ ከተመለሰ በኋላ ጉዳዩን በረቀት እየተከታተለች ምፍትሄ የሚገኝበትን መንገድ ስታፈላልግ ፓትርያርኩ አቡነ ዮሳብ ህዳር 4 ቀን 1949 ዓም ከዚህ አለም በሞት ተለዩ። በዚህም መሰረት በእርሳቸው መንበር የሚተካውን ፓትርያርክ ለመምረጥ የኢትዮጵያ ቤተክርስትያን መራጭ ወኪሎችን እንድትልክ ግብዣ መጣላት። ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስትያን በፓትርያርክ ምርጫ ላይ ያላት አግባብ በግልፅ ያልተወሰነ በመሆኑ ባለፉት ፓትርያርክ ላይም ያደረጋችሁት አድራጎት ጥሩ ባለመሆኑ እናዝናለን በማለት ግብዣውን እንደማትቀበለው አሳወቀች።

በዚህም ምክንያት የሁለቱ ቤተክርስትያኖች ግንኙነት ተቋርጦ ቆየ። ነገር ግን አዲሱ የተሾሙት ፓትርያርክ ባልተጠበቀ ሁኔታ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስትያን መዓረግ ወደ ፓትርያርክነት ደረጃ ከፍ ለማድረግ ያሰቡ መሆናቸውን የሚያትት ደብዳቤ አስይዘው ሦስት ጳጳሳትና አራት ምእመናን ወደ አዲስ አበባ ላኩ።

መልእክተኞችም አዲስ አበባ ላይ ከቤተ ክህነትና ከቤተ መንግስት ሰዎች ጋር ሰፊ ውይይት ሲያደርጉ ከሰነበቱ በኋላ ወደ አንድ ስምምነት በመድረስ የውል ስምምነት በሁለቱ ቤተ ክርስትያኖች መካከል ተፈረመ። በስምምነቱ መሰረት በወቅቱ የኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳሳት የነበሩት ብፁዕ አቡኔ ባስልዮስ ሰኔ 21 ቀን 1951 ዓም በብፁዕ አቡነ ቄርሎስ ተቀብተው የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ፓትርያርክ ሆነው ተሾሙ። በስነ ስርዓቱም ላይ ግርማዊ ንጉሠ ነገስቱ ቀዳማዊ ኃይለ ስላሤ ተገኝተው ነበር።

በዚህም ወቅት 21 መድፍ ተተኮሰ። በአዲስ አበባ የሚገኙ አድባራትና ገዳማት በደወል ድምፅ ደስታቸውን አሰሙ። ምእመናንም በእልልታ አጀቧቸው።

ምንጭ
ዜና ጳጳሳት ኢትዮጵያውያን (ዲ/ን መርሻ አለሀኝ)
https://am.sewasew.com/p/የኢትዮጵያ-ኦርቶዶክስ-ተዋህዶ-ቤተክርስትያን-የፓትርያርክ-ስልጣኗን-ለማግኘት-ከግብፅ-ቤተክርስትያን-ጋር-ያረገቸው-ተጋድሎ-ምን-ይመስል-ነበር-የመጀመሪያው-ኢትዮጵያዊ-ፓትርያርክስ-ማን-ናቸው

Want your school to be the top-listed School/college in Fremont?
Click here to claim your Sponsored Listing.

Address

Fremont, CA
Other Education Websites in Fremont (show all)
masters-call.net masters-call.net
Fremont, 94555

Audio & video archive collection of The World Teachers Trust

Complexquestion.Com Complexquestion.Com
Fremont

Complex Question is a question and answer site for common questions that are not so common for others. No registration. http://www.complexquestion.com/

Ohlone College Tutoring Services Ohlone College Tutoring Services
43600 Mission Boulevard
Fremont, 94539

In-person and Online Tutoring Services offered in Bldg. 3, Level 5 at the Ohlone College, Fremont

Sewasew Love & Relationship Sewasew Love & Relationship
Fremont

Bringing Africa's knowledge to the Internet!

IKIDZ Online IKIDZ Online
Fremont, 94536

Online After School Program GK-6 Online Summer Camps GK-6 Online Enrichment Activities GK - 12

Sewasew Culture Sewasew Culture
Fremont

Bringing Africa's knowledge to the Internet!

Kushal C: Language Videos Kushal C: Language Videos
Fremont, 94539

Hello! My name is Kushal Chattopadhyay, and I am a Bengali-American high school student very passion

Jain GuruKul of ARJ Jain GuruKul of ARJ
Fremont, 94538

Pranaam We are planing to craft the foundation of Jain Dharma in Daily lives. Through various way a

Nexus Fission Nexus Fission
Fremont

All things technical learning videos, latest tech, latest in stocks and other learnings too

Adults with Disabilities - Noll Center Adults with Disabilities - Noll Center
4700 Calaveras Avenue
Fremont, 94538

The Adults with Disabilities (AWD) Program offers life skills instruction for developmentally disabled adults. We teach skills that enable individuals to function independently and...

Storybook Express Storybook Express
47110 Havasu Street
Fremont, 94539

A project with the goal of providing underprivileged communities with free reading materials

Henry Harvin Henry Harvin
Sector 6 B 12
Fremont

Henry Harvin is a global education technology company